ባንኩ የመጀመሪያውን ሩብ ዓመት ስብሰባ አካሄደ

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የመጀመሪያውን ሩብ ዓመት ስብሰባ ጥቅምት 18 እና 19 ቀን 2010 ዓ.ም. አካሄደ።

  

 የበጀት ዓመቱ የ1ኛው ሩብ ዓመት የሥራ አፈፃፀም ሪፖርት በስትራቴጂ፣ ለውጥና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ቀርቦ በከፍተኛና መካከለኛ የማኔጅመንት አባላት ዘንድ ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል፡፡ በሁለተኛው ቀን ውሎው ደግሞ የባንኩ የብድር ፖሊሲ ረቂቅ ላይ ውይይት ተካሂዶ ግብዓቶች ተወስደዋል፡፡

በሩብ ዓመቱ በባንኩ የተመዘገበው የሥራ አፈጻጸም ውጤት በቂ (Satisfactory) የሚባል ሲሆን በዚህም በፕሮጀክትና ሊዝ ፋይናንሲንግ ብር 2.10 ቢሊዮን መፈቀዱ፣ ብር 1.43 ቢሊዮን መለቀቁና ብር 1.21 ቢሊዮን ደግሞ መሰብሰቡ በሪፖርቱ ተመላክቷል።   

ምርታቸውን ወደ ውጭ አገር የሚልኩ ተበዳሪዎች  በበጀት ዓመቱ ውስጥ ብር 352.2 ሚሊዮን የውጭ ምንዛሪ ገቢ አስገኝተዋል፡፡

ባንኩ በዓመቱ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ቦንድን በመሸጥ 628 ሚሊዮን የሚጠጋ ብር ሰብስቧል፡፡

  

 

በሩብ ዓመቱ ውስጥ ጤናማነታቸው የተጠበቁ ፕሮጀክቶች እየቀነሱ መምጣት፣ ወደ ውጭ ከሚላኩ ምርቶች የተሻለ የውጭ ምንዛሪ ማግኘት አለመቻል፣ የተበላሹ ብድሮች መጨመር እና የተበላሹ ብድሮች እንዲያገግሙ ማድረግ ያለመቻል፣ የፕሮጀክቶች ክትትል ማነስ፣ የቦንድ ሽያጭ በተመለከተ በተለይ በዲስትሪክቶችና ቅርንጫፎች በቂ ትኩረት አለመስጠት፣ የደንበኛህን እወቅ (KYC) ሥራ በአግባቡ አለመሥራት እና የመሳሰሉት በውይይቱ ወቅት እንደ ድክመት ተነስተዋል፡፡

ከውይይቱ በኋላ አቶ ጌታሁን የተበላሹ ብድሮችን ከመቀነስ አኳያ እንዲሁም ለውሳኔ ስለሚረዳ የፕሮጀክቶች ክትትል ሥራ ትኩረት ተሰጥቶት እንዲሰራ አጽንዖት በመስጠት ስብሰባውን ቋጭተዋል፡፡

በተያዘው በጀት ዓመት ባንኩ በፕሮጀክት ፋይናንሲንግ እና ሊዝ ፋይናንሲንግ ብር 14.03 ቢሊዮን ለመፍቀድ፣ ብር 9.99 ቢሊዮን ብድር ለመልቅና ብር 6.09 ቢሊዮን ለመሰብሰብ እንዲሁም ብር 378.65 ሚሊየን የተጣራ ትርፍ ለማግኘት ዕቅድ ይዞ በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡