የህዳሴ ግድብ የመሠረት ድንጋይ የተጣለበትን 7ኛ ዓመት አስመልክቶ የቴሌቪዥን ቶክ ሾው ተካሄደ

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ከታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ም/ቤት ጽ/ቤት እና ከኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ጋር በመተባበር “የታላቁ ህዳሴ ግድብ ቦንድ ጠቀሜታና ተግዳሮቶች” በሚል ርዕስ ያዘጋጀው የቴሌቪዥን ቶክ ሾው የካቲት 01 ቀን 2010 ዓ.ም. በኢንተርኮንቲነንታል ሆቴል ተካሄደ፡፡

የቶክ ሾዉ ዓላማ በቦንድ ግዥና አመላለስ ዙሪያ ኅብረተሰቡ በቂ ግንዛቤ እንዲኖረው ለማድረግ እንዲሁም በባለድርሻ አካላት መካከል ያለውን የመናበብና የመቀናጀት ችግር ለመቅረፍ ታስቦ ነው፡፡

 

ለውይይት መነሻ የሚሆኑ ጽሑፎች በኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፋይናንስና ባንኪንግ ም/ፕሬዝዳንት አቶ እንዳልካቸው ምኅረቱ እና በገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ባለሙያ አማካይነት ቀርበዋል፡፡

በቀረቡት ጽሁፎች ቁጠባ ለአንድ  አገር  ኢኮኖሚ ዕድገት  የሚኖረው ጠቀሜታ፣ ባለፋት ዓመታት ከቁጠባ ቦንድ ጋር ተያይዞ የቁጠባ ባህል እያደገ መምጣቱ፣ የቁጠባ ቦንድ ልዩ ባህርያትና የሽያጭ ሂደቱ ምን እንደሚመስል በአሃዝ ተደግፎ ቀርቧል፡፡

አቶ እንዳልካቸው ባቀረቡት መረጃ እስከ አሁን ከታላቁ ህዳሴ ግድብ 9.3 ቢሊዮን ብር በሽያጭ መሰብሰቡንና ከዚህ ውስጥ ደግሞ የመክፈያ ጊዜያቸው በመድረሱ 2.2 ቢሊዮን ለቆጣቢዎች ተመላሽ መደረጉን ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም እስካሁን ድረስ ከ200 ሺህ በላይ የሚሆኑ ሰዎች የታላቁን ኅዳሴ ግድብ ግንባታን በአካል እንደጎበኙት ተብራርቷል፡፡  የታላቁ ህዳሴ ግድብ ቦንድ ከኢኮኖሚ ጠቀሜታው ባሻግር በኅብረተሰቡ ዘንድ መቀራረብንና አንድነትን እንዲሁም የይቻላል መንፈስን መፍጠሩ ተጠቅሷል፡፡

የቀረቡ ጽሑፎችን ተከትሎም በተደረገው ውይይት የቦንድ ሽያጭ ላይ መቀዛቀዝ መታየቱ፣ ግድቡ 63 ከመቶ ብቻ የተጠናቀቀ በመሆኑና በኢትዮጵያውያን ብቻ የሚሰራ በመሆኑ ድጋፉ መቀጠል እንዳለበት ለዚህም በየደረጃው ያለው አመራር ሚናውን እንዲወጣ ማድረግ እንደሚገባ፣ በተከታታይ ኃላፊነታቸውን በመወጣት በአርያነት የሚነሱ ተቋማት እውቅና ሊሰጣቸው እንደሚገባ፣ ቦንድ የሚሸጥባቸው ቦታዎች በተለየ አቀራረብ ደንበኞችን በመሳብ ሽያጩን ማከናወን እንደሚጠበቅባቸው፣ የሁሉም ዓይነት የቦንድ መጠኖች በመሸጫ ቦታዎች መገኘት እንደሚኖርባቸው፣ ባለሃብቱ በቦንድ ግዥ የሚፈለገውን ያህል ተሳትፎ ማድረግ እንዳለበት፣ ም/ቤቱ የጉብኝት ፕሮግራሞችን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚኖርበት፣ መገናኛ ብዙኃንም ትኩረት ሰጥተው በተከታታይ መስራት እንዳለባቸው ተነግሮ ቶክ ሾዉ ተጠናቋል።

በመድረኩ ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ፣ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፣ ገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት፣ መከላከያ ሚኒስቴር፣ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን፣ የየም ልዩ ዞን፣ የፖለቲካ ፖርቲ ተወካዮች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ዩኒቨርስቲዎች፣ የአዲስ አበባ ዕድሮች ህብረት እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡