ኤልሲ አዲስ ከመታመም ወደ ማገገም፣ ከማገገም ወደ ትርፋማነት ተሸጋገረ!

ኤልሲ አዲስ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ (ELSE Addis Industrial Development) ባለሀብቶቹ ጥለውት ከሄዱ በኋላ በባንኩ በተደረገለት የማኔጅመንትና የቴክኒክ ድጋፍ ከጽኑ ህመሙ አገግሞ ወደ ትርፋማነት መሸጋገሩን የፋብሪካው ዋና ሥራ አሥኪያጅ አቶ ደሳለኝ ፍሬው ገለጹ፡፡

ባንኩ ፋብሪካውን ከተረከበ በኋላ ተጨማሪ በጀት መድቦለት፣ የማጅመንትና የቴክኒክ ድጋፍ አድርጎለት ወደ መደበኛ የማምረት ሥራው መመለሱን እና በባለሀብቶቹ ትዕዛዝ ተበትነው የነበሩ ከ900 በላይ ሠራተኞችም ወደ መደበኛ ሥራቸው መመለሳቸውን ዋና ሥራ አሥኪያጁ ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ፋብሪካው ለ24 ሰዓታት በማምረት ሂደት ላይ እንደሚገኝ እና ባለፉት ሁለት ወራት ብቻ ከብር 54 ሚሊዮን በላይ ጨርቃ ጨርቆችን ሸጦ ከብር 5.5 ሚሊዮን በላይ ትርፍ ማስመዝገቡን ገልጸዋል፡፡

“ኤልሲ አዲስ ከህመሙ አገግሞ በዚህ ደረጃ ትርፋማ የሆነው የሚያመርታቸውን ምርቶች ምንም እሴት ሳይጨምር ሙሉ በሙሉ ለሀገር ውስጥ ገበያ ብቻ እየሸጠ ባለበት ወቅት ነው” ያሉት ዋና ሥራ አሥኪያጁ “በምርቶቹ ላይ እሴት እየጨመረ ወደ ውጭ ቢልክ ደግሞ ትርፉ ከእጥፍ በላይ እንደሚጨምር እና ለዚህም ዕቅድ ተይዞ እየተሠራበት እንደሚገኝ” ጠቁመዋል፡፡

  

ለጊዜው የፋብሪካው የጨርቃ ጨርቅ ማሽኖች መለዋወጫ በሀገር ውስጥ አለመገኘቱና ከውጭ ለማስገባትም ጊዜ የሚወስድ መሆኑ እንዲሁም የጥጥ አቅርቦት አለመኖር ክፍተት እየፈጠረ ከመሆኑ ሌላ መሠረታዊ የሚባል ችግር እንደሌለ የገለጹት ዋና ሥራ አሥኪያጁ የባንኩ ዋና ዓላማ ፋብሪካውን እያስተዳደረ መቀጠል ሳይሆን ያሉበት ችግሮች ተቀርፈውና  ከህመሙ አገግሞ በትርፋማነቱ ለሦስተኛ ወገን ማስተላለፍ እንደሆነ አስገንዝበዋል፡፡ በለቀቁት የቱርክ ከፍተኛ ባለሙያዎች ምትክም ሕንዳውያን ባለሙያዎች ተቀጥረው ለኢትዮጵያውያን ሠራተኞች ማሽኖቹን ለማንቀሳቀስ የሚያስችል ተግባራዊ የሙያ ሥልጠና እየሰጡ መሆኑንም አቶ ደሳለኝ አክለው ገልጸዋል፡፡

ኤልሲ አዲስ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ (ELSE Addis Industrial Development Project) በኢትዮጵያ ልማት ባንክ የብድር ድጋፍ ተደርጎለት በሁለት የቱርክ ባለሀብቶች ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ካፒታል በአዳማ ከተማ የተቋቋመና ጨርቃ ጨርቅ በማምረት ላይ የሚገኝ ግዙፍ ፋብሪካ ነው፡፡ ቱርካውያን ባለሀብቶች የነበረባቸውን የብድር ዕዳ በውሉ መሠረት መመለስ ባለመቻላቸው፣ ሠራተኞቹን በትነው ፋብሪካው ምርት እንዲያቆም የማድረግ ሕገ-ወጥ ሙከራ በማድረጋቸው፣ የሠራተኞችን የሥራ ግብር ለመንግስት ገቢ ባለማድረጋቸው፣ ከደንበኞቻቸው ጋር ከፍተኛ የውዝፍ ዕዳ ውስጥ በመግባታቸውና በደረቅ ቼክ በማጭበርበራቸው፣ በመጨረሻም ሀገር ጥለው በመጥፋታቸው ምክንያት ባንኩ የአዋጅ ቁጥር 97/98 አግባብን ተከትሎ በመረከብ እያስተዳደረው ይቆያል፡፡