የዲስትሪክቶች የማበደር ጣሪያ ከፍ አለ

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የዲስትሪክቶች የማበደር ጣሪያ ከፍ ማለቱን የካቲት 21 ቀን 2010 ዓ.ም. በባንኩ ፕሬዝዳንት ተፈርሞ በወጣ የውስጥ ማስታወሻ ተገልጿል፡፡


የዲስትሪክቶች ማበደር ጣሪያ ከፍ እንዲል ምክንያት የሆነው በአገሪቱ ያለው የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ እያደገ መምጣቱ፣ የገንዘብ ምንዛሪ መውረድና የኢንቨስትመንት ወጪ መጨመር፣ የገበያ ሁኔታ መለዋወጥ፣ ለደንበኞች የተቀላጠፈ አገልግሎት በቅርበት ለመስጠት እና እርካታ ለመጨመር እንዲሁም የባንኩን ወጪ ለመቀነስ  እንደሆነ ተብራርቷል፡፡

ስለሆነም አዲስ አበባ፣ አዳማ፣ መቀሌ፣ ሐዋሳ እና ባሕር ዳር ዲስትሪክቶች እስከ ብር 45 ሚሊዮን፣ ነቀምት፣ ጅማ፣ ደሴ እና ድሬዳዋ ዲስትሪክቶች እስከ ብር 40 ሚሊዮን እንዲሁም ወላይታ ሶዶ፣ ጋምቤላ፣ ጎንደር እና ቡታጅራ ዲስትሪክቶች እስከ ብር 35 ሚሊዮን ድረስ እንዲያበድሩ መወሰኑ ታውቋል፡፡ 

ብድር የመፍቀድ ጣሪያቸው ከብር 45 ሚሊዮን በታች የሆኑ ዲስትሪክቶች ብድር የማቅረብ አቅሙ ከፍ ወዳለው በአቅራቢያቸው ወደሚገኝ ዲስትሪክት እንዲሄዱ እንዲሁም ከብር 45 ሚሊዮን በላይ የሆነ ጥያቄ ደግሞ ለዋናው መ/ቤት እንደሚቀርብ ተጠቁሟል፡፡

ይህ ውሳኔ እ.ኤ.አ. ከማርች 1 ቀን 2018 ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚደረግና በዚሁ መሠረት የዋና መ/ቤት አበዳሪ ክፍሎች ከዚህ ቀን ጀምሮ እስከ ብር 45 ሚሊዮን የሚደርሱ አዲስ የብድር ጥያቄዎችን ማስተናገድ እንዲያቆሙ፣ ሆኖም ከዚህ ቀደም የተቀበሏቸውን የብድር ጥያቄዎች እንዲያስተናግዱና ብድሩ ጸድቆ ውል ለመዋዋልና ለቀጣይ የፕሮጀክቱ አፈጻጸም ክትትል ወደ ሚመለከታቸው ዲስትሪክቶች እንዲልኩ፣ እስከ ብር 45 ሚሊዮን የሚደርሱ በዋናው መ/ቤት አበዳሪ ክፍሎች እጅ በሥራ (operational) እና በትግበራ (under implementation) ላይ የሚገኙ ፕሮጀክቶች እ.ኤ.አ. ከሐምሌ 1/2018 ጀምሮ ወደ ዲስትሪክቶች እንዲተላለፉ፣ እስከዚያው ድረስ ግን አሁን ባሉበት አስፈላጊው ክትትልና ድጋፍ እንዲደረግ ውሳኔ መተላለፉ በውስጥ ማስታወሻው ተገልጿል፡፡

ከዚህ ቀደም የነበረው የዲስትሪክቶች የማበደር ጣሪያ ለፕሮጀክት ፋይናንሲንግ እስከ ብር 25 ሚሊዮን እንዲሁም ለሊዝ ፋይናንሲንግ እስከ ብር 30 ሚሊዮን ድረስ ብቻ እንደነበረ ይታወቃል፡፡