የቦንድ ሽያጭ ሣምንት በይፋ ተጀመረ

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የመሠረት ድንጋይ የተጣለበት ሰባተኛ ዓመት የሕዳሴ ቦንድ ሽያጭ ሣምንት መጋቢት 10 ቀን 2010 ዓ.ም. በአዲስ አበባ አራዳ ጊዮርጊስ ምኒልክ አደባባይ በይፋ ተከፈተ።

 

 

 

 

ሥነ ሥርዓቱን በይፋ የከፈቱት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ክቡር ዶ/ር ታቦር ገ/መድኅን ሲሆኑ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችን ጨምሮ የመንግስት ባለሥልጣናት፣ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽ/ቤት ኃላፊዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በቦታው ተገኝተዋል፤ የታላቁን ሕዳሴ ግድብ ቦንድም በመግዛት አርዓያነታቸውን አሳይተዋል፡፡

የዕለቱ የክብር እንግዳ በመክፈቻ ንግግራቸው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የመሠረት ድንጋይ ከተጣለበት ዕለት አንስቶ እስካሁን ድረስ የፋይናንስ፣ የቴክኒክና የሀሳብ ድጋፍ ላደረጉ ተቋማትና የሕብረተሰብ ክፍሎች ምስጋናቸውን አቅርበው ይህ ድጋፍ የግድቡ ግንባታ ፍጻሜውን እስኪያገኝ ድረስ እንዲቀጥል ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ልማት ባንክም የቦንድ ሽያጭ ሣምንቱ የመክፈቻ ሥነ ሥርዓት በተሳካ ሁኔታ እንዲካሄድ ሙሉ በሙሉ ወጪውን የሸፈነ ሲሆን ባንኩም ለዚሁ ዓላማ ተብለው በተተከሉ ድንኳኖች በመገኘት የቦንድ ሽያጭ ማከናወን ጀምሯል።

የዕለቱ የክብር እንግዳ ክቡር ዶ/ር ታቦር ገ/መድኅን የሪባን ቆረጣ ሥነ ሥርዓቱን አከናውነው የቦንድ ሽያጭ ሳምንቱን በይፋ ያስጀመሩ ሲሆን ቦንድ በመግዛትም አርዓያነታቸውን አሳይተዋል።

በተጨማሪም ባንኩ የህብረተሰቡን ግንዛቤ ይበልጥ ለማሳደግ እንዲሁም የሚሰጠውን አገልግሎት ለማስተዋወቅ ያስችለው ዘንድ ስለ ቦንድ ምንነት እና ጠቃሚነት የሚያስተዋውቁ የቦንድ ብሮሸሮችን፣ በራሪ ወረቀቶችን፣ ፖስተሮችንና ባነሮችን በማሰራጨት ላይ ይገኛል።

የቦንድ ሽያጭ ሣምንቱ “ታላቁ የሕዳሴ ግድባችን የሀገራችን ሕብረ-ዜማ የሕዳሴችን ማማ!” በሚል መሪ ቃል ከመጋቢት 10-17 ቀን 2010 ዓ.ም. ድረስ በመላ አገሪቱ በተተከሉ የመሸጫ ጣቢያ ድንኳኖች በመከናወን ላይ ይገኛል።