ባንኩ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጠ

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ባለፉት አምስት ዓመታት ያከናወናቸውን ዋና ዋና ሥራዎች፣ የብድር አሰጣጡን እና አሰራሩን እንዲሁም በባንኩ አሠራር ላይ በሚነሱ ጉዳዮች ዙሪያ ለሚዲያ አካላት መስከረም 18 ቀን 2011 ዓ.ም. በኢንተርኮንቲነንታል ሆቴል ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል፡፡ 

  

የጋዜጣዊ መግለጫው መሰጠት ዋነኛ ዓላማ ባንኩ ባለፉት አምስት ዓመታት ያከናወናቸውን ዋና ዋና ሥራዎችን፣ የብድር አሰጣጡን እና አሰራሩን እንዲሁም በባንኩ አሠራር ላይ በሚነሱ ጉዳዮች ዙሪያ ለሚዲያ በመግለጽ እና ኅብረተሰቡ ዘንድ በማድረስ አሁን ያለውን አሉታዊ ገጽታ በበጎ ጎኑ እንዲገነባ ለማድረግ መሆኑን የባንኩ ፕሬዝዳንት አቶ ኃይለየሱስ በቀለ በመግቢያ ንግግራቸው ገልጸዋል፡፡

 በመቀጠል የባንኩ የአምስት ዓመት አፈጻጸም ምን እንደሚመስል፣ ዋና ዋና ችግሮች እና የተወሰዱ የመፍትሔ አቅጣጫዎች ምን እንደሆኑ የሚገልጽ ጽሑፍ በባንኩ የስትራቴጂ፣ ለውጥና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ክፍሌ ኃ/ኢየሱስ ቀርቧል፡፡

በጽሑፉ የባንኩ አደረጃጀት፣ አሰራርና የተቋቋመበት ዓላማ ከሌሎች ንግድ ባንኮች የተለየ መሆኑ፣ የባንኩን መስፈርቶች የሚያሟላ ማንኛውም ተበዳሪ እኩል አገልግሎት በፕሮጀክት ፋይናንስ እና በሊዝ ፋይናንስ ማግኘት እንደሚችል፣ የብድር አገልግሎት ዘርፎችም በመስኖ የሚለሙ ሰፋፊ የግል እርሻ ልማት ፕሮጀክቶች፣ የእርሻ ውጤቶች ማቀነባበሪያ፣ አምራች ኢንዱስትሪዎች፣ የማዕድንና ማዕድን ውጤቶች ኢንዱስትሪዎች፣ የማምረቻ ዕቃዎች ኪራይ መሆናቸው ተብራርቷል፡፡ 

ከዚህ በተጨማሪ የባንኩ የሥራ አፈጻጸም ውጤት ባለፉት አምስት ዓመታት (እ.ኤ.አ. ከ2013/14 እስከ 2017/18) ምን እንደሚመስል ተገልጿል፡፡ በዚሁ መሠረት የባንኩ አጠቃላይ ሀብት ከብር 35.7 ቢሊዮን ወደ ብር 78.18 ቢሊዮን ማደጉ፣ ያለበት የብድር መጠን ከብር 24.26 ቢሊዮን ወደ 70.13 ቢሊዮን ከፍ ማለቱ፣ የሰጠው አጠቃላይ ብድር ከብር ከ21.43 ቢሊዮን ወደ 39.15 ቢሊዮን ማደጉ፣ የተበላሸ ብድር ምጣኔ ከ9.95 በመቶ ወደ 39.43 በመቶ ማሻቀቡ፣ የባንኩ የተጣራ ትርፍ እንዳገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ እንዲሁም እንደየፕሮጀክቶቹ ዓይነት ከፍና ዝቅ ሊል እንደሚችል፣ የታላቁ ህዳሴ  ቦንድ ሽያጭ ባለፉት አምስት ዓመታት ብር 6.35 ቢሊዮን መድረሱ፣ ባንኩ ብድር በሰጣቸው ፕሮጀክቶች አማካይነት ለአገሪቱ የተገኘው የውጭ ምንዛሪ መጠን ብር 8.64 ቢሊዮን መሆኑ እንዲሁም በተመሳሳይ የተፈጠረው የሥራ ዕድል ብዛት 137,546 ያህል እንደሆነ በጽሑፉ ተመላክቷል፡፡

ከዚሁ ጎን ለጎን ባንኩ ውስጣዊ አደረጃጀቱንና አሰራሩን ከማሻሻል አኳያ ያከናወናቸው በርካታ ተግባራት መኖራቸው ተብራርቷል፡፡ በመሆኑም የተለያዩ ጥናቶች ተካሂደው ከባንኩ ሠራተኞች፣ ተበዳሪዎችና ባለድርሻ አካላት ጋር በየደረጃው ውይይቶች ከተካሄደባቸው በኋላ ማሻሻያዎች እንደተደረገባቸው ተጠቁሟል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በባንኩ የብድር እና የሊዝ ፋይናንሲንግ ፖሊሲዎችና መመሪያዎች ላይ ማሻሻያዎች ተደርገዋል፡፡

 በቀረበው ጽሑፍ እንደ ችግር የተነሱት ተቋማዊ የአፈጻጸም ዉሱንነቶች፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረት፣ የተበላሸ ብድር ምጣኔ እየጨመረ መምጣት፣ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት የተሟላ አለመሆን እና በሀገሪቱ ተከስቶ የነበረው አለመረጋጋትና የጸጥታ ችግሮች ናቸው፡፡ 

ባንኩ በቀጣይ ሊሰራ ያስቀመጣቸው አቅጣጫዎች ደግሞ በጥናት ላይ የተመሰረተ ሁሉንአቀፍ ለውጥ ለማድረግ የውጭ አማካሪዎችን በመጠቀም እንቅስቃሴ መጀመሩ፣ የባንኩን የፋይናንስ አቅም ለማጠናከር ለምሳሌ የባንኩን ካፒታል ለማሳደግ እርምጃዎች እየተወሰዱ መሆኑ፣ መንግስትን ጨምሮ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ተቀራርቦ በመስራት በልማት ፕሮጀክቶች ላይ የሚታዩ ችግሮችን መፍታት እንዲሁም ባንኩን በሚመለከት የተሳሳቱና የተዛቡ መረጃዎችን በማስተካከል የባንኩን ገጽታ መገንባት የሚሉት ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡ 

ከጽሑፉ በመቀጠል የተለያዩ ጥያቄዎች ከሚዲያ አካላት ተነስተው ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡ ከተነሱት ጥያቄዎች መካከል ባንኩ ለውጥ አመጣለሁ የሚለው ምን ያህል ታዓማኒነት እንዳለው ምክንያቱም በባንኩ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የጥቅም ግንኙነት/ኔትዎርክ/ አለ ስለሚባል፣ የተበላሹ ብድሮች /NPLs/ መጠን ከዓመት ዓመት እያሻቀቡ መምጣታቸው እንዲሁም የባንኩን አሰራር ለማዘመን በውጭ ኩባንያ ይጠናል የተባለው የትኛው ድርጅት እንደሆነ የሚታወቅ ነገር ካለ? የሚሉ ነበሩ፡፡

በመጨረሻ የባንኩ ፕሬዝዳንት ለተነሱት ጥያቄዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል፤ በዚሁ መሠረት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከንግዱ ማኅበረሰብ ጋር ባዘጋጀው ውይይት ላይ ይህ የጥቅም ግንኙነት የሚለው ሀሳብ ተነስቶ እንደነበር አስታውሰው ባንኩ ብድር ሲሰጥ እንደ ሌሎች ንግድ ባንኮች ቋሚ የሆነ ዋስትና /ኮላተራል/ እንደማይዝና በሚቀርበው የአዋጭነት ጥናት ላይ ብቻ ተመስርቶ እንደሆነ እና ይህን ለማረጋገጥ የሚኬድባቸው ብዙ መንገዶች እንዳሉ ከእነዚህም ውስጥ አንዱ የደንበኛህን እወቅ ጥናት /Due Diligence/ እንደሆነ፣ በፕሮጀክት ብድር አሰጣጥ ረገድ ደግሞ በባንኩ ውስጥ የዳበረ ልምድ እንዳለ ጠቁመዋል፡፡

ከተበላሹ ብድሮች /NPLs/ መጠን መጨመር ጋር በተያያዘ ለተነሳው ጥያቄ ሲመልሱ የውጭ ምንዛሪ እጥረት እና የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት አለመኖር እንዲሁም መቆራረጥ ችግሮች ከተፈቱ እና አሁን በሀገሪቱ የሰፈነው ጸጥታ ዘላቂነት ካለው ችግሩ ጊዜያዊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ባንኩ የተበላሹ ብድሮችን መጠን ለመቀነስ ለልማት ፕሮጀክቶች ተጨማሪ የእፎይታ እና የብድር መክፈያ ጊዜ እንዲሁም ሥራ ላይ ለሚገኙ ፕሮጀክቶች ደግሞ ተጨማሪ የብድር ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ፣ ከዚሁ ጎን ለጎንም መጠኑን ለመቀነስ ባንኩ ኢትዮ ካፒታል ኢንቨስትመንት የሚባል ድርጅት አቋቁሞ በመሥራት ላይ መሆኑን ገልጸው ትኩረት መደረግ ያለበት ግን የፋይናንስም ሆነ የቴክኒክ ድጋፉ ምን ያህል ለአገሪቱ ኢኮኖሚ አስተዋጽኦ አበርክቷል የሚለው እንደሆነ አጽንዖት ሰጥተዋል፡፡ 

ከዓለም አቀፍ አጥኚዎች ጋር በተያያዘም Terms of Reference መዘጋጀቱንና ውድድሩ በግልጽ ጨረታ ወጥቶ የሚካሄድ በመሆኑ ለወደፊቱ እንደታወቀ የሚገለጽ ይሆናል ብለዋል፡፡