የባንኩ ሠራተኞች በሀገር አቀፉ የችግኝ ተከላ መርኃ ግብር ላይ ተሳተፉ

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ማኔጅመንትና ሠራተኞች ሐምሌ 22 ቀን 2011 ዓ.ም. በሀገር አቀፍ ደረጃ በተካሄደው የችግኝ ተከላ መርኃ ግብር ላይ ሀገር በቀል ችግኞችንና የማስዋቢያ እጽዋትን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ ጉለሌ ክፍለ ከተማ፣ ወረዳ 10 በሚገኘው እና ባንኩ ከዚህ ቀደም ሙሉ የገንዘብ ድጋፍ ባደረገበት እጽዋት ማእከል በመገኘት ተሳትፈዋል፡፡

በእለቱ የባንኩን ፕሬዚዳንት አቶ ኃይለየሱስ በቀለን ጨምሮ የማኔጅመንት አባላትና ሠራተኞች፣ የጉለሌ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ፍስሃ ክፍለ እና የክፍለ ከተማው ሥራ አስፈጻሚዎችና ሠራተኞች ተገኝተው ሀገር በቀል ችግኞችን ተክለዋል፡፡

አቶ ኃይለየሱስ በቀለ በእለቱ ባስተላለፉት መልእክት ባንኩ 15,000 የሚደርሱ ችግኞችን ለመትከል እየተንቀሳቀሰ እንደሆነና ይህም የመጀመሪያው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከባንኩ እሴቶች መካከል አንዱ “ለአካባቢ ጥበቃ ትኩረት እንሰጣለን” የሚል ሲሆን ባንኩ በፕሮጀክት ፋይናንሲንግ ከ110 ዓመት በላይ የዳበረ ልምድ ያለው እና ተበዳሪዎች ከባንኩ ብድር ለማግኘት ሲፈልጉ አስቀድሞ ማሟላት ካለባቸው መስፈርቶች መካከል አንዱ የአካባቢ ደህንነትና ጥበቃ ጥናት ማቅረብ መሆኑ ይታወቃል፡፡