ባንኩ ለሚዲያ አካላት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጠ

 

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ሰኔ 04 ቀን 2012 ዓ.ም. ለሚዲያ አካላት በኮቪድ-19 እና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ በኢንተርኮንቲነንታል ሆቴል ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል፡፡

 

 

የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ኃይለየሱስ በቀለ በአሁኑ ጊዜ በዓለምአቀፍም ሆነ በሀገራችን በተከሰተው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት በባንኩ ብድር የተቋቋሙ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ላይ የራሱን አሉታዊ ተጽእኖ ማሳደሩን ገልጸው ባንኩም የራሱን የፕሮጀክት ማገገሚያ ስልቶችን በማዘጋጀት እና ጤናማ የሆኑ ፕሮጀክቶች በመለየት፣ በባንኩ ሥራ አስፈጻሚ እና ሥራ አመራር ቦርድ ታይተው ተገቢው ድጋፍ እንዲደረግላቸው እና የልዩ ልዩ ማሻሻያዎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ውሳኔዎች መተላለፋቸውን ተናግረዋል፡፡

በተቋም ደረጃም የባንኩን ሠራተኞች እና ደንበኞች ከወረርሽኙ ለመከላከል የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች መሠራታቸውን፣ የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች (ሳኒታይዘር እና አልኮል) መከፋፈላቸውን፤ በሥራ ቦታ አካላዊ ርቀት ተጠብቆ እንዲሠራ መደረጉን፣ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብሎች መታደላቸውን እና በሥራ መግቢያና መውጫ ሰዓት የትራንስፖርት አገልግሎት መመቻቸቱን ገልጸዋል፡፡

ኮቪድ-19 የሚያደርሰውን ወረርሽኝ ለመከላከል እንዲቻል በሀገር አቀፍ ደረጃ ለተቋቋመው የኮቪድ-19 ግብረ ኃይል እንዲሁ የአምስት ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉን የባንኩ ፕሬዚዳንት ተናግረዋል፡፡

የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት (MFIs) እና የኅብረት ሥራ ማኅበራት ባጋጠማቸው የገንዘብ እጥረት እና የእነሱ ተጠቃሚ ለሆኑ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ደንበኞቻቸው በአነስተኛ ወለድ የብድር አቅርቦት እንዲስተናገዱ መደረጉን አቶ ኃይለየሱስ ጨምረው አብራርተዋል፡፡

በመጨረሻም ከእርሻ ብድሮች ጋር በተያያዘ እንዲሁም የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በባንኩ ገቢ ላይ ስላስከተለው ጉዳት እና በቀጣይ ምን ለመሥራት እንደታሰበ ከሚዲያ ባለሙያዎች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ ሰጥተዋል፡፡