50 ዓመት የጋብቻ የወርቅ ኢዮቤልዩ በዓልን ምክንያት በማድረግ የቦንድ ግዥ ተፈጸመ

ታዋቂው የፋይናንስ ባለሙያ አቶ ኢየሱስወርቅ ዛፉ እና ባለቤታቸው የ50ኛ ዓመት የጋብቻ የወርቅ ኢዮቤልዩ በዓላቸውን ምክንያት በማድረግ በባንኩ ዋናው መ/ቤት በአካል በመገኘት ከወለድ ነጻ የሆነ የአንድ ሚሊዮን ብር የቦንድ ግዥ ፈጽመዋል፡፡

በተያያዘም ኢንጂነር ተረፈ ራስወርቅ የዛሬ ስምንት ዓመት የ50ኛ ዓመት የጋብቻ የወርቅ ኢዮቤልዩን በማስመልከት በልጅ እና ልጅ ልጆቻቸው ሥም ለእያንዳንዳቸው የ50 ሺህ ብር የቦንድ ግዥ ፈጽመው የነበሩ ሲሆን አሁንም በልጃቸው ሥም የብር 350 ሺህ የቦንድ ግዥ ፈጽመዋል፤ በአጠቃላይ ቤተሰቡ ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ግዥ አከናውነዋል፡፡

በቦንድ ግዥ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ኃይለየሱስ በቀለ የህዳሴ ግድቡ ሙሌት ሥራ መጀመሩ ትልቅ ብሥራት መሆኑንና ለዚህም ባንኩ ከመጀመሪያው ጀምሮ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም በቅርቡ ለግድቡ ግንባታ የብር 5 ሚሊዮን ቦንድ ገዝቶ በስጦታ መለገሱን፣ ከሥራ መሪዎች ጀምሮ ከደመወዛቸው ላይ እያዋጡ እንደሚገኙ እና የግድቡ ግንባታ ሥራ ስላልተጠናቀቀ ለወደፊቱ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አብራርተዋል፡፡ በዚሁ ዓላማ አንጋፋዎቹ ሰዎች ባንኩ ድረስ በመምጣት የቦንድ ግዥውን በመፈጸማቸው ፕሬዚዳንቱ ከፍ ያለ ምሥጋና አቅርበዋል፡፡

አቶ ኢየሱስወርቅ ዛፉ የህዳሴ ጉዳይ የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ አስተዋጽዖ ያለበትና “አሻፈረኝ እምቢ የምትል ኢትዮጵያ ተፈጥራለች” በማለት የገለጹ ሲሆን ኢንጂነር ተረፈ ራስወርቅ በበኩላቸው “ግድቡ የእኛ ነው” የሚለው አባባል ትልቅ መልእክት ያዘለና ሁላችንንም የሚያስተሳስረን ነው ብለዋል፡፡