ሰራተኛ ማህበሩ አዲስ የሥራ አስፈጻሚ አባላትን መረጠ

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ሰራተኛ ማህበር 40ኛውን መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ የኮቪድ-19 መመሪያን በጠበቀ ሁኔታ መስከረም 28 ቀን 2013 ዓ.ም ያካሄደ ሲሆን ጉባዔው 48 አባላት ያሉትን የምክር ቤት አባላትና ከምክር ቤቱም መካከል ሰባትሥራ አስፈጻሚዎችን መርጧል፡፡ ጠቅላላ ጉባዔው ለምክር ቤቱ ከየዲስትሪክቱና ዋናው መ/ቤት የሥራ ክፍሎች አንድ አንድ ተወካዮችን መምረጡም ታውቋል።

ጉባዔው የሰራተኛ ማህበሩን የስራ አስፈጻሚ እና የኦዲት ኮሚቴ ሪፖርቶችን አድምጧል፡፡

ጉባዔው የተጀመረው በባንኩ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ዮሐንስ አያሌው የመክፈቻ ንግግር ሲሆን እርሳቸውም የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በሃገሪቱ ብቸኛው የልማት ባንክ ከመሆኑ አንጻር በሃገሪቱ የሚታየውን የገበያ ክፍተት በመሙላት እና ልማቱን በማፋጠን ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ሲያበረክት በጉዞው ሂደት በርካታ ውጣ ውረዶችን ማሳለፉን አውስተዋል፡፡

አያይዘውም ባንኩ በየጊዜው የሚያጋጥሙትን ፈተናዎች ለማለፍና ህልውናውን ለማስቀጠል በየጊዜው የሚያጋጥሙ ችግሮቻችን ላይ በግልፅ በመነጋገርና መፍትሔ በማምጣት ከችግር በመውጣት ረገድ የባንኩ ሰራተኛ ማህበር በየኔነት ስሜት ብዙ መስራት እንደሚጠበቅበት አብራርተው፣ ባንኩም በጥናት ላይ የሚገኙ ማበረታቻዎች እንደ ሰራተኛው ብቃትና ችሎታ ተግባራዊ እንዲደረጉ የተቻለውን ጥረት እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡

በመቀጠል ንግግር ያደረጉት የባንክና መድን ሰራተኞች ማህበራት ኢንዱስትሪ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ደስታ በርሔ ሲሆኑ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ስብሰባዎችን ማድረግ አስቸጋሪ በሆነበት ወቅት አስፈላጊውን ጥንቃቄ ወስዶ ይህን ስብሰባ ማካሄዱ፣ በተጨማሪም በባንኩ እና  በባንኩ ሰራተኛ ማህበር መካከል ለ12ኛ ጊዜ የህብረት ስምምነት እንዲከናወን በማድረጉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

በመቀጠልም እስካሁን በነበሩ ስራ አስፈፃሚ አካላት የተሰሩ ስራዎችን በማንሳትና በማመስገን ቀጣይ ወደ ስራ አስፈፃሚነት የሚመጡትም ከቀዳሚዎቹ ተሞክሮ በመውሰድ እና መልካም ልምዶች በማዳበር፣ ከዚህ ቀደም የነበሩ አሰራሮችን የበለጠ በማስተካከል ለተሻለ ስራ ዝግጁ እንዲሆኑ አሳስበዋል፡፡

ጉባዔው በአቶ ደስታ በርሔ አስመራጭነት የቀጣይ ስራ አስፈፃሚ አባላትን ምርጫ አካሂዷል፡፡ በምርጫውም፡- አቶ ይበልጣል ያየህ- ፕሬዚዳንት፣ አቶ አዲሱ ገብረ ሐና- ምክትል ፕሬዚዳንት፣ እንዲሁም አቶ ኃይሉ ተፈራ -ዋና ፀሐፊ ሆነው የተመረጡ ሲሆን የቀሩት ስራ አስፈፃሚ አባላት ደግሞ አቶ ግዛቸው ተክሉ፣ አቶ ኤርሚያስ አብድቄ፣ ወ/ሮ ኦሪት አበበ እና ወ/ሮ አዳነች ገረሱ ናቸው፡፡ በተጨማሪም ወ/ሮ ምህረት ኃ/የሱስ፣ አቶ መስፍን ሳህሌ እና አቶ ኢፋ ሽፈራው ደግሞ ለኦዲት ኮሚሽን ተመርጠዋል፡፡

በመጨረሻም የተመራጮች ቃለ መሃላ ሥነ ሥርዓት በማከናወን ስብሰባው ተጠናቋል፡፡