በባንኩ ስትራቴጂክ ሪፎርም እቅድ ዙሪያ ውይይት ተካሄደ

በኢትዮጵያ ልማት ባንክ የስትራቴጂክ ሪፎርም እቅድ ዙሪያ የአንድ ቀን ወርክሾፕ በቢሾፍቱ ከተማ ኩሪፍቱ ሪዞርት ተካሂዷል፡፡

 

በመንግስት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ አስተባባሪነት ጥር 22 ቀን 2013 ዓ.ም በተዘጋጀው በዚህ ወርክሾፕ ላይ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የገቢ፣ በጀትና ፋይናንስ ቋሚ ኮሜቴ አባላት፣ የኤጀንሲው የስራ ኃላፊዎች፣ የባንኩ ፕሬዝዳንትና ም/ፕሬዚዳንቶች እንዲሁም ሌሎች የስራ መሪዎች ተገኝተዋል፡፡

ወርክሾፑን የኤጀንሲው የኦፕሬሽን ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ክቡር አቶ ትዕግስቱ አምሳሉ የመክፈቻ ንግግር በማድረግ አስጀምረዋል፡፡

በንግግራቸውም የወርክሾፑ ዋነኛ ዓላማ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በብድር አሰጣጥ፣ ክትትልና አመላለስ ዙሪያ ያጋጠሙትን ችግሮች በመፍታት፣ የተቋቋመበትን ተልዕኮ ለማሳካትና ኃላፊነቱን በአግባቡ ለመወጣት እንዲያስችለው በተቀረጸው የአምስት ዓመት የስትራቴጂክ ሪፎርም ዕቅድ ዙሪያ ለተከበረው ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ አባላት ገለጻ ማድረግ ነው፡፡

የገለጻውም አስፈላጊነት የተከበረው ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ አባላት ድጋፍና ክትትል እንዲሁም የባለድርሻ አካላት ትብብር ለተቋሙ ሪፎርም ስኬት ወሳኝ ሚና የሚጫወት በመሆኑ በሁሉም ባለድርሻ አካላት ዘንድ በባንኩ ሪፎርም ስራ ላይ ወጥ የሆነ መግባባት እንዲፈጠር ማስቻል እንደሆነ ጨምረው ተናግረዋል፡፡

በመቀጠል የባንኩ ፕሬዚዳንት ዮሐንስ አያሌው /ፒ.ኤች.ዲ/ የተቋሙን የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ፣ ባንኩ እያከናወነ ያለውን መጠነ ሰፊ የሪፎርም ትግበራ፣ አሁን ላይ ስለሚገኝበት የለውጥ ሂደት እና ተግዳሮቶች ዙሪያ ገለጻ አድርገዋል፡፡

ገለጻውን ተከትሎ መድረኩ ለውይይት ክፍት የተደረገ ሲሆን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቋሚ ኮሜቴ አባላት ገንቢ የሆኑ ግብዓቶችንና አስተያየቶችን ሰጥተዋል፤ ላነሷቸው አንዳንድ ጥያቄዎችም ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡

ከተነሱ አስተያየቶች መካከል የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በተከበረው ምክር ቤት አባላት ዘንድ የነበረው አስተሳሰብ አሉታዊ እንደነበር በዚህም የባንኩን ቀጣይነት አስመልክቶም ቀደም ሲል በምክር ቤቱ አባላት ዘንድ ጥያቄ ውስጥ የገባ እንደነበር አስታውሰው ቋሚ ኮሚቴው ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ለማስረዳት ከፍተኛ አስተዋጽዖ ያደረገ መሆኑ ግንዛቤ ተወስዷል፡፡

በአሁኑ ጊዜ ባንኩ እያከናወነ ያለውን የሪፎርም ሥራ እንዲሁም እየሄደበት ያለው መንገድ ተቋሙን መለወጥ የሚያስችል እንደሆነ ገልጸው ሂደቱ ሊበረታታና ድጋፍ ሊሰጠው የሚገባ በመሆኑ ባንኩ እያከናወነ ያለውን የሪፎርም ሥራ ለሁሉም ባለድርሻ አካላት በማሳወቅ የገጽታ ግንባታ ሥራዎችን በትኩረት ሊሰራ ይገባል ብለዋል፡፡

በተያያዘ የምክር ቤቱ የቋሚ ኮሚቴ አባላት ለባንኩ የሪፎርም ትግበራ ስኬት በየጊዜው ተገቢውን ድጋፍና ክትትል እንዲሚያደርጉ ቃል ገብተዋል፡፡

ክቡር አቶ ትዕግስቱ አምሳሉ በበኩላቸው የኤጀንሲው ዋነኛ ትኩረት የመንግስት የልማት ድርጅቶች ውጤታማ እንዲሆኑ ማስቻልና ማገዝ በመሆኑ ተቋማቸው የሚጠበቅበትን ክትትልና ድጋፍ ለባንኩ ያደርጋል ብለዋል፡፡

በተጨማሪም በባንኩ በኩል አሁን እየታዩ ያሉት ለውጦች የሚበረታቱ መሆናቸውን አንስተው በተከበረው ምክር ቤት አባላት የተሰጡ አስተያቶችና ግብዓቶች ተወስደው እንዲሰራባቸው አቅጣጫ ሰጥተዋል፡፡

በወርክሾፑ ማጠቃለያ ላይ የባንኩ ፕሬዚዳንት ዮሐንስ አያሌው /ፒ.ኤች.ዲ/ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የገቢ፣ በጀትና ፋይናንስ ቋሚ ኮሚቴ አባላት ለባንኩ የሪፎርም ስራ ትኩረት በመስጠት በወርክሾፑ ላይ በመገኘታቸው ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡