የባንኩ BSC ወርክሾፕ ላይ የማጠቃለያ መርኃ ግብር ተካሄደ

ባንኩ ከየካቲት 08-17/2013 ዓ.ም ሲያካሂድ የነበረውን አዲስ የውጤት ተኮር ምዘና ስርዓት ስልጠና /BSC/ የማጠቃለያ መርኃ ግብር የካቲት 26 ቀን 2013 ዓ.ም በባንኩ የመሰብሰቢያ አዳራሽ አካሂዷል፡፡

 በማጠቃለያ መርኃ ግብሩ ላይ የባንኩ ፕሬዚዳንትን ጨምሮ ም/ፕሬዚዳንቶች ዳይሬክተሮችና የቡድን ሥራ አስኪያጆች የተገኙ ሲሆን፤ የዲስትሪክት እና  ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጆች በዙም /zoom meeting/ ስብሰባውን ተሳትፈዋል፡፡

ስብሰባውን በንግግር የከፈቱት የባንኩ ፕሬዚዳንት ዮሐንስ አያሌው /ፒ.ኤች.ዲ/ ሲሆኑ እንደርሳቸው ገለጻ ይህ የውጤት ተኮር ምዘና /BSC/ ወርክሾፕ ባንኩ ለጀመረው የሪፎርም ስራ አንዱ አጋዥ መሳሪያ ነው ብለዋል፡፡

ባንካችንን ደረጃውን የጠበቀ ባንክ /world class/ ለማድረግ የሚያስችል ቢዝነስ ሞዴል እየተዘጋጀ መሆኑን እንዲሁም ተግባራዊ እየተደረገ ባለው ባንኩ የጀመረውን ለውጥ ውጤታማ እንዲሆን ለማድረግ ሁሉም የስራ መሪና ሰራተኛ ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ እንደሚገባም ጨምረው ተናግረዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ ቀሪ ጊዜ ውስጥ የተጀመረውን የሪፎርም ሥራ በሚፈለገው ጥራትና ፍጥነት ለማከናወን በውጤት ተኮር የምዘና ሥርዓት /BSC/ መታገዝ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በተለይም ባንኩ የብድር አሰባሰብ ማሳደግ፣ የተበላሸ የብድር ምጣኔ መቀነስ፣ የተቀላጠፈ አገልግሎት መስጠት እና ጥራት ያለው የብድር አሰጣጥ ተግባራዊ ማድረግ ላይ በውጤት ተኮር የምዘና ሥርዓት ታግዞ መስራት ለውጤት እንደሚያበቃ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ መጨረሻም ሆነ በቀጣዮቹ ተከታታይ ዓመታት የባንኩን የተበላሸ የብድር ምጣኔ ለመቀነስ እንዲቻል የተጀመረውን ሪፎርም ስራ ማጠናከር እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የባንኩ የውጤት ተኮር ምዘና (BSC) ከባንኩ የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ ተቆርሶ እስከ ሠራተኛ ድረስ የሚወረድበት አሠራር ለመዘርጋት በከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲከለስ መደረጉን አብራርተዋል፡፡

 

የተከለሰውን የውጤት ተኮር ምዘና በአጭር ጊዜ ውስጥ ተግባራዊ ለማድረግ ይቻል ዘንድም በሶስት ማዕከላት ማለትም በባንኩ ዋና መ/ቤት፣ በባህርዳርና ሀዋሳ ስልጠናዎች ሲሰጡ እንደነበር ተናግረዋል፡፡

 

ለሪፎርሙ መሳካትም 7 ስትራቴጂክ ምሶሶዎች፣ 26 ስትራቴጂክ ዓላማዎች እና ቁልፍ የአፈፃፀም አመልካቾች ሠራተኛ ድረስ በማውረድ ባንኩ ውስጥ ግልጽነት እና ተጠያቂነት እንዲሰፍን ለማድረግ ታስቦ እየተሰራበት እንደሚገኝ አክለው ገልጸዋል፡፡