ክቡር ተገኝወርቅ ጌጡ (.ኤች.) የጃፓን ከፍተኛ የኒሻን ተሸላሚ ሆኑ!!

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ የሆኑት ክቡር ተገኝወርቅ ጌጡ (ፒ.ኤች.ዲ) በጃፓን መንግስት የኒሻን ሽልማት የተሰጣቸው እ.ኤ.አ ህዳር 03 ቀን 2020 ሲሆን፤ ሽልማቱን አስመልክቶ እ.ኤ.አ መጋቢት 24 ቀን 2021 በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር መኖሪያ ቤት በተዘጋጀው ሥነ ሥርዓት ላይ ተበርክቶላቸዋል፡፡

የሀገርቷ ከፍተኛ የኒሻን ሽልማት የተበረከተላቸው በጃፓን እና በአፍሪካ እንዲሁም በጃፓን እና በኢትዮጵያ መካከል ኢኮኖሚያዊ ግንኙነቶችን በማጠናከር ረገድ ላበረከቱት አስተዋጽዖ እንደሆነ በሥነ ሥርዓቱ ላይ ተገልጿል፡፡

በእርሳቸው አመራር ሰጭነት በአፍሪካ ልማት ዙሪያ በቶክዮ ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ አማካይነት ከጃፓን መንግስት ጋር ያለውን ኢኮኖሚያዊ ግንኙነቶች ወደ ላቀ ደረጃ በማድረስ በርካታ ቢሊዮን ዶላሮች ለአፍሪካ ልማት እንዲውል ተደርጓል፡፡

በተለይም እንደ ጃፓን የውጭ ንግድ ድርጅት (ጄትሮ)፣ የጃፓን ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጄንሲ (ጃይካ)፣ UNDP እና ከኬይዛይ ዶዩዩይ (የጃፓን የኮርፖሬት አስፈጻሚዎች ማህበር) ጋር የሽርክና ማዕቀፎችን በመፍጠር የአፍሪካ ሀገራት ከጃፓን መንግስት ጋር ስትራቴጂያዊ ግንኙነት እንዲፈጥሩና በኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ክቡር ተገኝወርቅ ጌጡ (ፒ.ኤች.ዲ) ከፍተኛ አስተዋጽዖ አበርክተዋል፡፡