የባንኩ ሠራተኞች በችግኝ ተከላ መርኃ ግብር ተሳተፉ

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ “ኢትዮጵያን እናልብሳት” በሚል መርህ እየተካሄደ በሚገኘው ሀገር አቀፍ የችግኝ ተከላ መርኃ ግብር ላይ ሐምሌ 10 ቀን 2013 ዓ.ም ተሳትፎ አድርጓል፡፡

የባንኩ የበላይ አመራር፣ የሥራ መሪዎችና ሰራተኞች ባንኩ ከዚህ ቀደም ባለማው ጉለሌ ክፍለ ከተማ በሚገኘው የእጽዋት ማዕከል በአካል በመገኘት፣ በባንኩ ውስጥና ዙሪያ ችግኞችንና የቤት ውስጥ የማስዋቢያ እጽዋት በመትከል ተሳትፎ አድርገዋል፡፡ እንዲሁ የጉለሌ ክፍለ ከተማ ሥራ አስፈጻሚዎችና ነዋሪዎች በችግኝ ተከላ መርኃ ግብሩ ላይ ተሳትፈዋል፡፡

የባንኩ ፕሬዚዳንት ክቡር ዮሐንስ አያሌው (ፒ.ኤች.ዲ) ባንኩ ባለማው እጽዋት ማእከል የችግኝ ተከላው መርኃ ግብር ከመካሄዱ አስቀድሞ የመክፈቻ ንግግር አድርገዋል፡፡ በንግግራቸው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በልዩ ሁኔታ ለአረንጓዴ አሻራ ትኩረት በመስጠት በጉለሌ እፅዋት ማዕከል አካባቢ ቦታ በመረከብ ከብር 15 ሚሊዮን በላይ ወጪ አድርጎ ያለማው ውብ የባንኩ አረንጓዴ መናፈሻ ፓርክ ኢትዮጵያን በማልበስ ሂደት ውስጥ ያለንን መልካም ጅምርና ቁርጠኝነት ያሳያል ብለዋል፡፡

ባንኩ በዛሬው ዕለት ከጉለሌና ቂርቆስ ክፍለ ከተሞች ጋር በመተባበር በዋናው መስሪያ ቤት ግቢና ቀደም ብሎ ባንኩ ባለማው የጉለሌ እፅዋት ማዕከል ውስጥ 3,675 ችግኞችንና የግቢ ማስዋብ እፅዋቶች፣ እንዲሁም  በባንኩ የዲስትሪክት ጽ/ቤቶች አማካይነት ከ18,000 ችግኞች በመተከል ላይ ተተክለዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ባንኩ ለችግኝ ግዥ እና ሌሎች ተያያዥ ወጪዎች ለጉለሌና ቂርቆስ ክፍለ ከተሞች የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉን እንዲሁ ገልጸዋል፡፡  

የጉለሌ ክፍለ ከተማ አስተዳደር የብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ የተከበሩ አቶ ሲሳይ እንዳለ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ሀገራዊ ጥሪውን መሰረት በማድረግ አረንጓዴ አሻራውን ለማኖር ክፍለ ከተማውን መርጦ ተሳትፎ በማድረጉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

ባንኩ ይህንን ሀገራዊ የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ከመደገፍ አኳያ ለቂርቆስና ጉለሌ ክፍለ ከተሞች ለችግኝ ተከላ መርኃ ግብር እንዲሆናቸው የፋይናንስ እገዛ ከማድረጉ በተጨማሪ ለገጽታ ግንባታ ይሆነው ዘንድ የባንኩን ስምና ዓርማ የያዙ የማስተዋወቂያ ቁሳቁሶችን ማለትም ኮፍያ እና ሳኒታይዘር እስክሪብቶዎችን አሰራጭቷል፡፡