የባንኩ ሠራተኛ ማኅበር 42ኛ መደበኛ ስብሰባውን አካሄደ

"ሠራተኛው በማኔጅመንቱ እንዲተማመን እንፈልጋለን" - አቶ ሰፊዓለም ሊበን

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ መሠረታዊ ሠራተኛ ማኅበር ሐምሌ 15 ቀን 2013 ዓ.ም 42ኛ መደበኛ የምክር ቤት ስብሰባውን በባንኩ ዋና መስሪያ ቤት አዳራሽ አካሂዷል፡፡

 

በማኅበሩ መደበኛ ስብሰባ ላይ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የባንኩ ምክትል ፕሬዝዳንት-ኮርፖሬት አገልግሎት አቶ ሰፊዓለም ሊበን ናቸው፡፡

“የሠራተኛውን መብት ማስጠበቅ ለተቋሙ ሕልውና ወሳኝ ነው፣ የሠራተኛውን መብት ለማስጠበቅ ደግሞ በማኅበር መደራጀት አስፈላጊ ነው” ያሉት አቶ ሰፊዓለም በአሁኑ ሰዓት የባንኩ ከፍተኛ ማኔጅመንት መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣትና ውጤታማ ጉዞን ለማስቀጠል ቆርጦ በመነሳት ሌት ተቀን እየሠራና አበረታች ትርፍም እያስመዘገበ መሆኑን ጠቁመው “ሠራተኛው በማኔጅመንቱ እንዲተማመን እንፈልጋለን፣ ተደራጅቶ እስካገዘንና ባንኩ በውጤታማነት እስከቀጠለ ድረስ በሂደት እየተጠና የማይከበርለት መብትና የማይመለስለት ጥያቄ አይኖርም” ብለዋል፡፡

በተለይም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የሠራተኛ ማኅበሩ ሥራ አስፈጻሚዎችና የባንኩ ከፍተኛ አመራሮች የበለጠ ተቀራርበው መሥራት በመጀመራቸው የሠራተኛው ፍላጎት በተሻለ መልኩ መመለስ መጀመሩና ባንኩም በውጤታማነት ቀጣይነቱን ማረጋገጡ ትልቅ ትርጉም የሚሰጠው ነው ብለዋል ምክትል ፕሬዚዳንቱ፡፡

ባንኩ በዚህ ዓመት ውጤታማ የሆነው ከፍተኛ አመራሩ የወሰዳቸውን ስትራቴጂካዊ ውሳኔዎች ሠራተኛው ደግፎ ለለውጥ ስለተንቀሳቀሰ መሆኑን ተናግረው ለወደፊቱም ለተሻለ ውጤት እንደሚረባረብ ያላቸውን ጽኑ እምነት ገልጸዋል፡፡

የሠራተኛ ማበህሩ ሊቀመንበር አቶ ይበልጣል ያየህ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ባንካችን ላስመዘገበው የላቀ ውጤት  የእንኳን  ደስ አላችሁ መልክት ካስተላለፉ  በኋላ ለዚህ ውጤት መመዝገብ ከፍተኛውን ሚና ለተጫወቱ የባንኩ ከፍተኛ የማኔጅመንት አባላት በሠራተኛው ስም ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ ውጤቱ የተመዘገበው ከባንኩ ከፍተኛ የስራ አመራር አባላት ጠንክራ ሥራ በተጨማሪ የባንኩ ሰራተኞችም የተሰጣቸውን ኃላፊነት በሚገባ በመወጣታቸው ጭምር በመሆኑ የባንኩ ሰራተኞችም ምስጋና እንደሚገባቸው ገልፀዋል፡፡

በዚህ 42ኛው የምክር ቤት ጉባዔም የሠራተኛ ተወካዮች በሆኑ የምክር ቤት አባላት መነሳት የሚገባው ጉዳይ ባንኩ ባስመዘገበው ውጤት በመበረታታት የባንኩን ዘላቂ ውጤታማነት ለማምጣት ከፊት መቆም እንደሚጠበቅ መገንዘብ እንደሚገባ አንስተዋል፡፡ ምክንቱም እንደ ሠራተኛ ማኅበር ተወካይነታችን የሠራተኛው ጥቅም እንዲከበር የምንፈልግ ከሆነ የባንካችንን ውጤታማነት ማረጋገጥ አስፈላጊ በመሆኑ ሁሉም ሠራተኛ በትጋት መስራት ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡

ባንኩ ውጤታማ እሰከሆነ ድረስ ደግሞ የሠራተኛው ጥቅምና መብት እንዲከበር ማህበሩ ጠንክሮ እንደሚሰራና የባንኩ የበላይ አመራርም ተመሳሳይ አቋም እንዳለው፣ ለዚህም ቃል እደተገባላቸው አውስተዋል፡፡ ከዚህ በፊት በሠራተኛው በተደጋጋሚ የሚቀርቡ ጥያቄዎችን በተመለከተ ማህበሩ ለባንኩ ማኔጅመንት በጽሑፍና በቃል በማቅረብ የውሳኔ ሐሳብ እየተጠባበቀ እንደሚገኝ አስታውሰው የባንኩ የሪፎርም እና ሪስትራክቸሪንግ ስራዎች እንደተጠናቀቁ የባንኩ ከፍተኛ ስራ አመራር  ሠራተኛውን የሚጠቅም መልስ እንደሚሰጡ ሙሉ ተስፋ እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ፋይናንስ ተቋማት ኢንዱስትሪ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ደስታ በርሔ በበኩላቸው ባንኩ ያስመዘገበው ለውጥ ሁላችንም ከገመትነው በላይ ነው፡፡ ይህም የባንኩን አመራርና የሠራተኛውን ተግባብቶ መሥራት የሚያመለክት ነው፡፡ በመሆኑም ይህን ለውጥ በብቃት ለመሩትና ቃላቸውን በተግባር ለተረጎሙት የባንኩ ከፍተኛ አመራሮች አድናቆትና ምስጋና አቅርበዋል፡፡

ከባንኩ ዲስትሪክት ጽ/ቤቶች ሠራተኛውን ወክለው ስብሰባውን የታደሙት ተወያዮችም ለምክትል ፕሬዚዳንቱ በርካታ ጥያቄዎችን አንስተው ማብራሪያ ተሰጥቷቸዋል፡፡ እነዚህም፡- በቤት ብድር መመሪያ ዙሪያ፣ በአበል አከፋፈል፣ ደመወዝና የደረጃ እድገት ፣ዝውውር፣ በበረሃማ አካባቢ የሚሠሩ ሠራተኞች ጥቅማጥቅምና የቦታ ለውጥ፣ ከቤተሰብ ሕክምና፣ ወዘተ፣ ጋር የተያያዙ ጥያቄዎች ተነስተው ውይይት ተደርጎባቸዋል፤ ምላሽም ተሰጥቶባቸዋል፡፡

ከሠራተኛ ተወካዮች ለተነሱ ሐሳቦች ማብራሪያ የሰጡት አቶ ሰፊዓለም ሁሉም ጥያቄዎች ትክክለኛና መልስ የሚፈልጉ መሆናቸውን አስምረውበት ሆኖም ሁሉም በአንድ ጊዜ ሊመለስ ስለማይችል የተጀመሩ መልካም መሻሻሎችን እውቅና በመስጠት ላልተመለሱት በጋራ መሥራት ይገባል ብለዋል፡፡ የሠራተኛው መብት በዘላቂነት እንዲከበርና ጥቅማጥቅሙ እንዲጠበቅለት ከተፈለገ አብዛኞቹ ጥያቄዎች በጥናት መመለስ እንዳለባቸው አስረድተዋል፡፡ መመሪያ ሲወጣም ሆነ አሠራር ሲዘረጋ የባንኩ ዋና አላማ ሠራተኛውን ተጠቃሚ ማደረግና ለውጤታማነት ማነሳሳት እንጅ ሌላ ስላልሆን የሠራተኛውን ችግር የማይፈቱና ለተጨማሪ ቅሬታ በር የሚከፍቱ መመሪያዎችና አሠራሮችም ተለይተው የማይሻሻሉበት ምንም ምክንያት የለም ብለዋል፡፡

የሠራተኛ ማኅበሩ 42ኛ መደበኛ የምክር ቤት ስብሰባ አንዳንድ የፕሮቶኮል ውሳኔዎችን በማሳለፍና እና የቀድሞ የማኅበሩ አመራሮችን በክብር በመሸኘት ተጠናቋል፡፡