የፀረ-ሙስና ቀን ተከበረ

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ሠራተኞችና ማኔጅመንት አባላት በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ18ኛ ጊዜ፣ በሀገራችን ደረጃ ደግሞ ለ17ኛ ጊዜ የተከበረውን የፀረ-ሙስና ቀን በባንኩ የመሰብሰቢያ አዳራሽ በሥነ ምግባር የታነፀ አመራር ከሙስና ለፀዳች ኢትዮጵያ!በሚል መሪ ቃል ህዳር 30 ቀን 2014 .ም አክብረዋል፡፡

 

በሥነ ሥርዓቱ ላይ የባንኩ ፕሬዝዳንት፣ ምክትል ፕሬዚዳንቶች፣ የማኔጅመንት አባላት እና ሠራተኞች የተገኙ ሲሆን ለውይይት መነሻ የሚሆኑ ጽሑፎችም ለውይይት ቀርበዋል፡፡

በሥነ ሥርዓቱ መጀመሪያ ላይ የባንኩ ፕሬዝዳንት ክቡር ዮሐንስ አያሌው (.ኤች.) ባደረጉት ንግግር “በሥነ ምግባር የታነፀ አመራር ከሙስና ለፀዳች ኢትዮጵያ!” በሚል መሪ ቃል በዓሉን ስናከብር እኛም በሥነ ምግባራችን የታነፅን ሆነንና ለሌሎች አርአያ በመሆን ኃላፊነታችን በአግባቡ በመወጣት የባንካችንን ሥም እና ዝና ከፍ ልናደርግ ይገባል ያሉ ሲሆን አያይዘውም በቀጣይም የባንካችን ኃላፊዎች እና ሠራተኞች በሥነምግባር የታነፁ እና ሙስናን የሚፀየፉ እና የሚታገሉ እንዲሆኑ ለማስቻል እንደ ብድር ሥራ ሁሉ የሥነ ምግባር ግንባታ ላይ በትኩረት የሚሰራ ሲሆን፣ በአጥፊዎች ላይ የሚወሰደው የእርምት እርምጃም የተጠናከረ ይሆናል ብለዋል፡፡

የፍልስፍና ሚና በፀረ-ሙስና ጉዞ” በሚል ርዕስ በ/ር ዳኛቸው አሰፋ እንዲሁም በባንኩ ውስጥ ሙስናና ብልሹ አሰራርን ከመከላከል አንጻር የሥነ ምግባር ክፍሉ ያከናወናቸው ተግባራት እና ሙስናና ሥነ ምግባር የወቅቱ ቁልፍ ጉዳዮች በሚል ርዕስ በአቶ ወርቁ ፈቃደ የባንኩ የሥነ ምግባርና ቅሬታ መከታተያ ቢሮ ሥራ አስኪያጅ ለውይይት መነሻ የሚሆን ጽሑፍ ቀርቦ በተሳታፊዎች ውይይት ተደርጎበታል፡፡

በመጨረሻም የባንኩ ፕሬዚዳንት ይህን በዓል ስናከብር ሙስናና ብልሹ አሰራር በሀገርና ተቋማት ላይ የሚያስከትለውን ተጽዕኖ በውል ተገንዝበን፣ ከመከላከል አንጻር የራሳችንን ድርሻ ወይም አስተዋጽ ተረድተን ኃላፊነታችንን መወጣት ይኖርብናል ያሉ ሲሆን እንደ ተቋም የኢትዮጵን ኢኮኖሚ የማሳደግ ኃላፊነት ተሰጥቶናል፡፡ ግልፅ የሆነ ራዕይና ተልዕኮም አስቀምጠናል፡፡ በዚህ ውስጥ የእኔ ድርሻ ምንድን ነው ብለን መጠየቅ ይኖርብናል፤ የባንኩ ሠራተኞችም በውሎው የተነሱ መልእክቶችን ከእለት ተእለት መደበኛ ሥራቸው ጋር በማዛመድ ተግባራዊ እንዲያደርጉ አሳስበዋል፡፡