በባንኩ የገንዘብ ድጋፍ የተገነቡ የአቅመ ደካሞች መኖሪያ ቤቶች ተመረቁ

 

በኢትዮጵያ ልማት ባንክ የገንዘብ ድጋፍ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5 ፈርሰው እንደ አዲስ የተገነቡ 5 የአረጋዊያንና አቅመ ደካሞች መኖሪያ ቤቶች፣ 4 መጸዳጃ ቤቶች እና 1 ምግብ ማብሰያ ቤት ጥር 14 ቀን 2014 .ም ተመርቀው የቁልፍ ርክክብ ሥነ ሥርዓት ተካሂዷል፡፡

በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የባንኩ ፕሬዚዳትና ምክትል ፕሬዚዳንቶች እንዲሁም የቂርቆስ ክፍለ ከተማ እና የወረዳ 5 ከፍተኛ የሥራ አመራር አባላት ተገኝተዋል፡፡

የባንኩ ፕሬዚዳንት ዮሐንስ አያሌው (.ኤች.) በሥነ ሥርዓቱ ላይ ባስተላለፉት መልእክት ይህ ተግባር ባንኩ በማኅበራዊ ኃላፊነት ከሚያደርጋቸው መጠነ ሰፊ ድጋፎች መካከል አንዱ ሲሆን ባንኩ ከተቋቋመበት 1901 .ም ጀምሮ ማኅበራዊ ኃላፊነቱን በልዩ ልዩ መንገዶች ሲወጣ የኖረ የሀገር ሀብትና ኩራት የሆነ አንጋፋ ባንክ ነው ብለዋል፡፡

ባንኩ በራሱ በየዓመቱ በጀት እየያዘ ከሚያደርጋቸው ድጋፎች በተጨማሪ የፋይናንስ ድጋፍ የሚያደርግላቸው ፕሮጀክቶች ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ሲያደርግ መኖሩ ይታወቃል፡፡ በኢትዮጵያ ልማት ባንክ በኩል ተግባራዊ የሚደረጉ ፕሮጀክቶች በዋናነት እንዲያካትቷቸው ከሚገደዱባቸው መስፈርቶችም አንዱ ማኅበራዊ ኃላፊነትን የሚወጡበት አሠራር መሆኑን አውስተዋል፡፡

የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሙባረክ ከማል በበኩላቸው ባደረጉት ንግግር የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ክፍለ ከተማው የአረጋውያኑን ቤት ለማደስ ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ ሲያቀርብ ለሰጠው ቀና ምላሽ በተለይም ቤቶቹን በክፍለ ከተማው እስካሁን ከተደረጉ የቤት እድሳቶች እጅግ በተለየ መልኩ በከፍተኛ ጥራት ሰርቶ ከማስረከብ ባለፈ ለባለቤቶቹ መሠረታዊ የቤት ቁሳቁስ እንዲሟላ በማድረጉ መደሰታቸውን ገልፀው ለዚህም ባንኩ ከፍተኛ ምስጋና ይገባዋል ብለዋል፡፡

በመጨረሻም የባንኩ ፕሬዚዳንት ለነዋሪዎቹ የቤቶቹን ቁልፎች ለነዋሪዎቹ ያስረከቡ ሲሆን ቁልፉን የተረከቡ ነዋሪዎችም በተደረገላቸው ድጋፍ መደሰታቸውን ገልጸም ለባንኩ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ ክፍለ ከተማውም ለባንኩ የምሥጋና ምሥክር ወረቀት አበርክቷል፡