በጉለሌ ክ/ከ በባንኩ የገንዘብ ድጋፍ የተገነቡ የአቅመ ደካሞች መኖሪያ ቤቶች ተመረቁ

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 እና ወረዳ 8 በባንኩ የገንዘብ ድጋፍ እንደ አዲስ ፈርሰው የተገነቡ 3 የአረጋውያን እና አቅመ ደካሞች መኖሪያ ቤቶች ጥር 21 ቀን 2014 ዓ.ም ለነዋሪዎቹ ተላልፈዋል፡፡

በተዘጋጀው የቤት ምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ የባንኩ ፕሬዚዳትና ምክትል ፕሬዚዳንቶች እንዲሁም የጉለሌ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚን ጨምሮ ሌሎች የክፍለ ከተማውና ወረዳ አመራሮች ተገኝተዋል፡፡

በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የባንኩ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ዮሐንስ አያሌው (ፒ.ኤች.ዲ) ባደረጉት የመክፈቻ እና የእንኳን ደስ አላችሁ ንግግር የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ማኅበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት በዚህ ዓመት ብቻ 120 ሚሊዮን ብር መድቦ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ገልፀው የዚሁ ማህበራዊ ኃላፊነት አንዱ አካል የሆነው የአቅመ ደካሞችና አረጋውያን ቤቶችን መገንባት መሆኑን ተናግረው፤ ለወደፊቱም ባንኩ ድጋፋን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አክለው ገልጸዋል፡፡

የጉለሌ ክ/ከ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ቆንጂት ደበላ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በክፍለ ከተማው እያከናወነ ያለው ተግባር ባንኩ የህዝብ ባንክ ለመሆኑ ማሳያ ነው ያሉ ሲሆን፤ በአሁን ሰዓት ለነዋሪዎቹ ላደረገው አስተዋጽዖ አመስግነው ድጋፉ ቀጣይነት እንደሚኖረው ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡

በጉለሌ ክ/ከ ቤቱ ተገንብቶ የተሰጣቸው አረጋውያን ከዚህ ቀደም ይኖሩበት የነበረው ቤት ፍፁም ለኑሮ ምቹ እንዳልነበር ገልጸው፤ በአሁኑ ጊዜ ባንኩ ገንብቶ የሰጣቸው ቤት እና የቤት ቁሳቁስ ኑሯቸውን የቀየረ በመሆኑ መደሰታቸውን ገልፀው ባንኩ ላደረገላቸው ድጋፍ ምሥጋና አቅርበዋል፡፡ ክፍለ ከተማውም ለባንኩ የምሥጋና ምሥክር ወረቀት ሰጥቷል፡፡

ከዚህ ቀደም ባንኩ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ያስገነባቸውን የአቅመ ደካሞች መኖሪያ ቤቶችን እንደ አዲስ አፍርሶ በመሥራት ለነዋሪዎቹ ማስረከቡ ይታወሳል፡፡