የባንኩ የሕንፃ ግንባታ የመሠረት ድንጋይ ተቀመጠ

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የአዳማ ዲስትሪክት ሊያስገነባው ላቀደው ሁለገብ ሕንጻ የተዘጋጀው የመሠረት ድንጋይ የባንኩ ከፍተኛ ሥራ ኃላፊዎችና አዳማ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ በተገኙበት ሰኔ 1 ቀን 2014 ዓ.ም ተቀመጠ፡፡

በ208 ሚሊዮን ብር ወጪ እንዲሠራ የታቀደለት ይኸው ሕንፃ ባለ ስምንት ወለል ሕንፃ ሆኖ ምድር ቤትና ግራውንድ የሚኖረው ሲሆን፣ የባንኩ የአዳማ ዲስትሪክት ለደንበኞቹ የሚሰጠውን አገልግሎት ለማቀላጠፍ አንደሚያስችል የታመነበት ነው፡፡

የመሠረት ድንጋዩ በተጣለበት በዚህ ሥነ ሥርዓት ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የባንኩ የኮርፖሬት ዘርፍ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሰፊ ዓለም ሊበን በንግግራቸው እንዳመለከቱት   ባንኩ ደንበኞችን ለማገልገል ምቹና ቀልጣፋ አገልግሎትን ከማምጣት ባሻገር የሠራተኞች ካፍቴሪያና የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታ /gymnasium/፣ የመሰብሰቢያ አዳራሾች ወዘተ የሚኖሩት ሲሆን፣ ከባንኩ አሠራር ጋር በማይጋጭ መንገድ ተጨማሪ ገቢ የሚያስገኙ የሚከራዩ ሱቆችንም እንዲይዝ ተደርጎ የሚገነባ ይሆናል። የሕንፃ ግንባታው ከሁለት እስከ ሦስት ዓመታት ብቻ ሊወስድ አንደሚችል የጠቆሙት አቶ ሰፊዓለም የሕንጻው ዲዛይንም ባንኩ በሌሎች ክልሎች ለሚያስገነባቸው መሰል ሕንፃዎች እንደ ሞዴል ሊወሰድ እንደሚችልም ጠቁመዋል፡፡

በሥነ ሥርዓቱ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የከተማው ክንቲባ አቶ ኃይሉ ጀልዴ በበኩላቸው የአዳማ ከተማን ‹‹ስማርት›› ከተማ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ባለበት በዚህ ወቅት ልማት ባንክ ስሙን የሚመጥን እና ለልማት ያለውን አጋርነት በሚያሳይ መንገድ ይህን ሁለገብ ሕንፃ ለመሥራት መነሣቱን እናደንቃለን ብለዋል፡፡ ልማት ባንክ ለሚያከናውናቸው ተግባራትም የከተማ አስተዳደሩ ከጎኑ መቆሙን አረጋግጠዋል፡፡

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ አዳማን ጨምሮ ዋና ዋና ከተሞች በሚገኝ 12 ዲስትሪክቶችና 78 ቅርንጫፎች እንዳሉት ይታወቃል፡፡