የጀርመን ልማት ባንክ ቀጣናዊ ዳይሬክተር በሐዋሳ የሥራ ጉብኝት አደረጉ

የጀርመን ልማት ባንክ (KFW) የምሥራቅ አፍሪካና የአፍሪካ ኅብረት ቀጣናዊ ዳይሬክተር ሚስተር ክሪስቶፍ ቲከንስ ሰኔ 25 ቀን 2014 ዓ.ም በኢትዮጵያ ልማት ባንክ ሐዋሳ ዲስትሪክት በመገኘት የሥራ ጉብኝት አደረጉ፡፡

ሚስተር ክሪስቶፍ ከሌሎች የሚመለከታቸው ባለሥልጣናት ጋር ሐዋሳ በሚገኘው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ዲስትሪክት በደረሱበት ጊዜ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት ዮሐንስ አያሌው (ፒ.ኤች.ዲ) እና ሌሎች ከዋናው መሥሪያ ቤትና ከዲስትሪክቱ የተገኙ የማኔጅመንት አባላት ደማቅ አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡

ሚስተር ክሪስቶፍ ቲክንስ በሥራ ጉብኝታቸው የሐዋሳ ዲስትሪክት እና ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤቶች የሥራ ሁኔታ የጎበኙ ሲሆን፣ በዕለቱ በጀርመን ልማት ባንክ የገንዘብ ድጋፍ ተገዝተው ለኢትዮጵያ ልማት ባንክ ደንበኞች ሊተላለፉ የተዘጋጁ የኮምባይነር ሃርቨስተር ቁልፍ ለደንበኞች የመስጠት ሥነ ሥርዓት ተካሂዷል፡፡ 

በዕለቱ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት እንግዶችን ‹‹እንኳን ደኅና መጣችሁ›› ለማለት ባደረጉት ንግግር የኢትዮጵያ መንግሥት የሀገሪቱን የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር በማሳካት በኩል ለግብርና ሜካናይዜሽን ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑንና በዚህ ፕሮጀክትም የሕዝቡን ሕይወት በመለወጥ ረገድ ፍሬ ማፍራት መጀመሩን ጠቅሰው፣ የጀርመን መንግሥትና የጀርመን ልማት ባንክ በኢትዮጵያ የግብርና ሜካናዜሽን ሊዝ ፕሮጀክትን በማቋቋም እያመጡት ላለው ውጤት ምስጋና አቅርበዋል፡፡ የኢትዮጵያ ልማት ባንክን በዚህ ጠቃሚ ፕሮጀክት ትግበራ ውስጥ ዋነኛ ተባባሪ አድርገው በመምረጣቸውም ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል፡፡ የግብርና ሚኒስቴር የሜካናይዜሽን ዳይሬክቶሬት በዚህ ፕሮጀክት ትግበራ ሂደት ያለውን ጉልህ ሚናም ተወስቷል፡፡ 

የጀርመን ልማት ባንክ በኢትዮጵያ የግብርና ሜካናይዜሽን እንዲስፋፋ ባለው አቋም 13 ሚሊዮን ዩሮ የፋይናንስ አቅርቦት በማድረግ እስከ አሁን 57 ያህል አገልግሎት ሰጪዎች(ኢንትርፕራዞች) ኮምባይነር ሃርቨስተሮችን በመረከብ ላይ ናቸው፡፡ ሌሎች በርካቶች ደግሞ ከዚሁ ድጋፍ ተጠቃሚ ለመሆን  ሂደት ላይ መሆናቸውም ታውቋል፡፡ በሐዋሳ ዲስትሪክት ሥር ያሉ ደንበኞችም በዚህ ረገድ ተጠቃሚ መሆናቸውም ተጠቁሟል፡፡   

ከዚሁ ጉብኝት ጋር ተያይዞም የጀርመን ልማት ባንክ ልኡካን ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ የማኔጅመንት አባላትና ከባንኩ ደንበኞች ጋር ባደረጉት  ውይይት የግብርና ሜካናይዜሽን ሊዝ ፕሮጀክት እያመጣ ያለውን ለውጥ ተመልክተዋል፡፡

በዚህም ፕሮጀክት ተጠቃሚ የሆኑ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ደንበኞች የጀርመን ልማት ባንክ የምሥራቅ አፍሪካ ዳይሬክተር ክሪስቶፍ ቲክንስ ፊት ያላቸውን ጥረትና የወደፊት ተስፋ አንጸባርቀዋል፡፡

በውይይት መድረኩ ከተገኙት ደንበኞች አንዱ የሆኑትና የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የባሌ ጎባ ቅርንጫፍ ጋር በቅርበት የሚሠሩት አቶ ሀብታሙ ሹሜ ‹‹ከባህላዊ አስተራረስ ወጥተን ዘመናዊ እርሻ እንዲስፋፋ በኢትዮጵያ ልማት ባንክና በጀርመን ልማት ባንክ ትብብር እየተተገበረ ያለው ግብርና ሜካናይዜሽን ፕሮጀክት ለውጥ አምጥቶልናል፤ ከፍተኛ ተጠቃሚም ሆነናል›› ብለዋል፡፡ 

ከባሌ የመጡት ሌላ የልማት ባንክ ደንበኛ አቶ ለገሰ ሙለታ በበኩላቸው ‹‹እርሻን ሜካናይዜሽን በመታገዝ የሥራ ዕድል ፈጥሬያለሁ፤ ዱቄት ፋብሪካ ለማቋቋም በቅቻአለሁ፤ ከፍተኛ አቅም አግኝቼአለሁ›› ብለዋል፡፡ በተመሳሳይ አቶ ረጋሳ ፈይሳም ‹‹ባሌ ገና ሊሠራ የሚችልበት ሰፊ መሬት አለ፤ አሁን እየተሰጠ ያለው ድጋፍ የሚደነቅ ነው፡፡ ሆኖም ገና ግን ብዙ ኮምባይነር ሃርቨስተር የሚፈልግ ሰፊ የእርሻ ልማት እምቅ አቅም አለ፤ ስለዚህ የጀርመን ልማት ባንክ ድጋፉን እንዲያሳድግ ያስፈልጋል›› ብለዋል፡፡

ውይይቱን በትኩረት የተከታተሉት ሚስትር ክሪስቶፍ ቲክንስ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ልማት ባንክና ማኔጅመንት፣ ሠራተኞች እንዲሁም ደንበኞች ባደረጉላቸው አቀባበልና የጉብኝት ሥነ ሥርዓት መደሰታቸውን፣ በጉብኝቱም ጠቃሚ ግብዓት ማግኘታቸውን ያረጋገጡ ሲሆን፣ ወደፊት ለበለጠ መሥራት የሚያስችል ድጋፍ ከጀርመን መንግሥት እንዲፈቀድ የበኩላቸውን  ለመወጣት ቃል ገብተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት ዮሐንስ አያሌውም (ፒ.ኤች.ዲ) በውይይቱ የተገኙ ሐሳቦች ጠቃሚ መሆናቸውን አረጋግጠው ወደፊት በውይይቱ የተንጸባረቁ ሐሳቦችን መሠረት አድርገው በጉድለት የሚጣዩ ነገሮችን ሁሉ ለማሟላት እንደሚሠሩ አስታውቀዋል፡፡