ቦርዱ ከሠራተኞች ጋር ስብሰባ አካሄደ

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የቦርድ ሥራ አመራር ከባንኩ ሥራ መሪዎችና ሠራተኞች ጋር ጥቅምት 26 ቀን 2ዐ12 ዓ.ም በኦሮሞ ባህል ማዕከል ስብሰባ አካሂዷል፡፡

የስብሰባው ዋና ዓላማ ከቦርዱ ጋር ትውውቅ ማድረግና ቦርዱ ያዘጋጀውን የ5 ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ ማቅረብ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የቦርድ ሥራ አመራር ሰብሳቢ ዶ/ር ተገኘወርቅ ጌጡ በስብሰባው መክፈቻ ላይ ባንኩ ከ11ዐ ዓመት በላይ በሆነው ዕድሜው ለአገራችን ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽዖ ማበርከቱን ገልጸው፤ እንደቻይና፣ ብራዚል፣ ህንድ እና ፈረንሳይ አሁን ለደረሱበት የኢኮኖሚ ማማ መሠረታቸው የልማት ባንኮቻቸው መሆናቸውንም አክለዋል፡፡ 

ሆኖም ልማት ባንክ እንደሌሎች ዓለም አቀፍ ባንኮች ተወዳዳሪ ሆኖ እንዲቀጥል ለማስቻል ቦርዱ የ5 ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ ማዘጋጀቱን፤ በዕቅዱ የባንኩን ታሪካዊ ዳራ፣ አሁን ያለበት አቋም እና በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ የት መድረስ እንዳለበት ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

 

 

በመቀጠል በባንኩ የቦርድ አባልና የቀድሞው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ ዶ/ር ዮሐንስ አያሌው የ5 ዓመቱን ስትራቴጂክ ዕቅድ (እ.ኤ.አ. ከ2019-2023) አቅርበዋል፡፡

በስትራቴጂክ እቅዱ ባንኩ ከሌሎች ንግድ ባንኮች የተለየ ስለመሆኑ፤ ከዚህ ቀደም የነበረው ቢዝነስ ሞዴል ከአሠራር፣ ገቨርናንስ እና መዋቅር አኳያ ክፍተቶች የነበሩበት በመሆኑ አዲስ የቢዝነስ ሞዴል እንደሚያስፈልገው ተብራርቶ ቀርቧል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የባንኩን 27% የብድር ድርሻ የያዙትን የጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪ ፕሮጀክቶችን አስመልክቶ የቦርድ አባልና የኢትዮጵያ ጨርቃጨርቅ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ስለሺ ለማ አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ኃይለየሱስ በቀለ በበኩላቸው ቦርዱ በአጭር ጊዜ ውስጥ ባንኩን በጥልቀት አጥንቶ ወደ ሥራ መግባቱን አድንቀዋል፡፡ ባለፈው በጀት ዓመት በብድር አሰባሰብ እና ክትትል ሥራ ላይ የነበሩ የሥራ ርብርብ ጥሩ እንደነበርም አክለዋል፡፡ ሆኖም ለብድር የተያዘ የመጠባበቂያ ወጪ /Provision/ አያያዝ ስርዓታችን መፈተሽ እንዳለበት እና በዓለም አቀፉ የሒሳብ ሪፖርት ሥርዓት /IFRS/ መሠረትም የምንሰራበት ይሆናል ብለዋል፡፡ 

በአጠቃላይ ቦርዱ ከያዘው ስትራቴጂክ ዕቅድና የለውጥ /ሪፎርም/ ሥራ ጋር በመሆን ባንኩ አሁን ካለበት ወደ ተሻለ ደረጃ ከፍ በማድረግ እናሻግረዋለን ብለዋል፡፡

በመቀጠል የቦርድ ሰብሳቢው መድረኩን ለተሰብሳቢዎች ክፍት አድርገው የተለያዩ አስተያየቶችንና ጥያቄዎችን ተቀብለዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል ቦርዱ ያዘጋጀው የ5 ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ ጥሩ እንደሆነና የባንኩ ሠራተኞች እቅዱን ከግብ ለማድረስ ተግተው እንደሚሰሩ፣ ባንኩን በአግባቡ ሊጠቅሙ የሚችሉ ሆኖም ትኩረት ያልተደረገባቸው የሥራ ክፍሎች ስለመኖራቸው፣ ከኑሮ ውድነቱ አንጸር የደመወዝማ ሻሻያ፣ የቦነስ እና እርከን ጭማሪ ጉዳይ፣ የባንኩን ገጽታ ለመገንባት ለሚዲያ ጋዜጣዊ መግለጫ መስጠት ስለማስፈለጉ፣ ከምደባ፣ ዝውውርና እድገት አኳያ ክፍተቶች እንዳሉ፣ የባንኩ ችግሮች አብዛኛው ምንጭ ከውጭ አካላት ስለመሆኑና የመሳሰሉት ናቸው፡፡

በመጨረሻም የቦርድ ሰብሳቢው የተነሱት ሀሳቦችና ጥያቄዎች ጥሩ እንደሆኑ እና በ5 ዓመቱ ስትራቴጂክ እቅዱ ውስጥ በዝርዝር እንደተቀመጡ፤ በሁሉም አቅጣጫ ባንኩን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ፣ ባንኩ ውጤታማ ከሆነ የሠራተኛ ጥያቄዎችን ማለትም ደመወዝ እና ሌሎች ጥቅማጥቅሞችን ከመመለስ ባሻገር በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ አዎንታዊ ሚና ማሳረፍ እንደሚቻል፤ ስለሆነም ሁሉም የባንኩ ሥራ አመራርና ሠራተኛ ተባብሮ በመሥራት ስትራቴጂክ እቅዱን ከግብ ማድረስ እንደሚጠበቅበት አቅጣጫ ሰጥተው ስብሰባውን ቋጭተዋል፡፡