ባንኩ ለሚዲያ አካላት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጠ

 

 

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የካቲት 19 ቀን 2012 ዓ.ም. ለሚዲያ አካላት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል፡፡

የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ኃይለየሱስ በቀለ በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ባንኩ አገራዊ ተልእኮውን በብቃት ለመወጣትና ኢኮኖሚውን ለመደገፍ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ፣ በዚህም  የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ሪፎርም እቅድ አዘጋጅቶ ወደ ትግበራ መግባቱን እና በስድስት ወሩ የሥራ አፈጻጸም ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በማብራሪያው ባንኩ በአዲስ አሠራር፣ አደረጃጀት እና የሪፎርም ጥናት ላይ መሠረት በማድረግ ወደ ሥራ በመግባቱ እ.ኤ.አ. 2018 ከተመዘገበው ኪሳራ ወጥቶ ትርፋማ መሆን መቻሉን የባንኩ ፕሬዚዳንት ገልጸዋል፡፡

የሪፎርም ዕቅዱ የተዘጋጀው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳን መሠረት በማድረግ፣  እንዲሁም የባንኩን ውስጣዊና ውጫዊ ነባራዊ ሁኔታዎችን በማጣጣም መቀረጹን፣ በዕቅዱ ሰባት ምሶሶዎች መኖራቸውን፣ እነዚህ እንዲሳኩም “ባንኩ አለማቀፋዊ ደረጃውን የጠበቀ ልማት ባንክ” እንዲሆን ማስቻል የሆነ ራዕይ ቀርጾ እየሠራበት እንደሚገኝ ጨምረው ተናግረዋል፡፡

በዚህም ባለፉት ሁለት ሩብ ዓመቶች (እ.ኤ.አ. ከሐምሌ 01 እስከ ታህሳስ 31, 2019) ባንኩ ብር 6.27  ቢሊዮን ወይም የእቅዱን 83% ፈቅዷል፤ ብር 4.4 ቢሊዮን ደግሞ የለቀቀ ሲሆን 77% ከእቅዱ ለማሳክት ችሏል፤ እንዲሁ ብር 4.51 ሰብስቧል ይህም የእቅዱን 118% ፈጽሟል፡፡ ይህ አፈጻጸም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በብድር መፍቀድ የ4% ጭማሪ፣ በብድር መልቀቅ የ7% ማነስ እና በብድር መሰብሰብ ደግሞ የ125% ብልጫ አሳይቷል ብለዋል፡፡

ባንኩ በተጠቀሰው ግማሽ ዓመት ከታክስ በፊት ብር 951.6 ሚሊዮን ትርፍ ሊያገኝ ችሏል፤ ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ228% ብልጫ አለው፡፡ በመሆኑም አሁን ያለው የባንኩ ጠቅላላ ሀብትም ብር 89.4 ቢሊዮን መድረሱን አብራርተዋል።

ባንኩ ትርፋማ መሆን የቻለው በመላው ሠራተኛው ርብርብ፡ አዲሱ የባንኩ ሥራ አመራር ቦርድ ከሥራ አስፈጻሚው ጋር በጥምረትና በመተጋገዝ በመሥራቱ ሲሆን የተበላሸ ብድር መጠንን በመቀነስ እና አዳዲስ ፕሮጀክቶች ወደ ተበላሸ ብድር ጎራ እንዳይገቡ በመግታት ጭምር መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በመቀጠልም ከሚዲያ ለተነሱ ጥያቄዎችም ምላሽ ሰጥተዋል፤ ከተነሱት ጥያቄዎች መካከል፡-የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ቢል /NBE Bill/፣ ብድር አቅርቦት እና አመላለስ፣ በአምስት ዓመቱ የስትራቴጂክ ሪፎርም እቅድ መጨረሻ የተበላሸ ብድር መጠንን በምን ያህል ለመቀነስ እንደታሰበ፣ ስለ አጠራጣሪ ብድሮች /NPLs/፣ በዝናብ ለሚለሙ እርሻዎች ብድር መቆሙ እና መቼ ለማስቀጠል እንደታሰበ፣ የውጭ ባለሃብቶች ከባንኩ ተበድረው ስለመጥፋታቸው እና ባንኩ ስለሚወስዳቸው እርምጃዎች፣ የፖሊሲው መሻሻል በልማቱ ላይ ያለው ፋይዳ እንዲሁም ከሊዝ ፋይናንሲንግን አገልግሎት ጋር በተያያዘ ናቸው፡፡

በምላሹም እስካሁን ድረስ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ብር 52 ቢሊዮን ብድር መወሰዱን፣ እንዲሁም ባንኩ ጊዜውን ጠብቆ ብር 32 ቢሊዮን መመለሱን፣ ለባንኩ ቀጣይነት ለመንግስት የተጨማሪ ካፒታል ጥያቄ መቅረቡን ተናግረዋል፡፡

የአጠራጣሪ ብድር /NPL/ መጠን 34% እንደደረሰ የተገለጸ ሲሆን በስትራቴጂው ሪፎርም እቅድ መጨረሻም ወደ 10% በመቶ ለማውረድ እቅድ ተይዞ እየተሠራ እንደሚገኝ፣ አጠራጣሪ ብድር /NPL/ ማለት ሙሉ በሙሉ የወደመ ወይም የማይመለስ ማለት እንዳልሆነ ተብራርቷል፡፡ ብድራቸውን ባልመለሱ ተበዳሪዎች እና ተባባሪ በአጥፊዎችም ላይ አስተዳደራዊና እና ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ፣ የእርሻ ብድሮች ሙሉ በሙሉ አለመቆማቸው ለማሳያ ለቡና እርሻ፣ አበባ፣ ወተት ልማት ፕሮጀክቶች እና በመስኖ ለሚለሙ እንደሚሰጥ፣  ፕሮጀክቶቻቸውን ጥለው ስለጠፉ ባለሃብቶች ንብረቱን ተረክቦ በማስተዳደር ላይ እንደሚገኝ፤ ለምሳሌ አይካ አዲስ ጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪ ከ4500 በላይ ሠራተኞች እንዳይበተኑ የራሱን ማኅበራዊ ኃላፊነት እየተወጣ ቢገኝም ቀደምት ባለሃብቶቹ ያልተከፈለ ፍሬ ግብር፣ የሠራተኛ የጡረታ መዋጮ፣ የመብራት እና የተለያዩ እዳዎች ባንኩ አብሮ እንደተረከበ ተብራርቷል፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘ የፖሊሲው ማሻሻያ ብዙ የሃገር ውስጥ ባለሃብቶችን የሚያበረታታ እንደሆነ፣ ከሊዝ ፋይናንሲንግ አገልግሎት ጋር በተያያዘም ባንኩ ወደዚህ ብድር ሲገባ በቂ ዝግጅት እንዳልነበረው ሆኖም ሥራው ውጤታማ እንዲሆን ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡