የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የቦንድ ሽያጭ ሣምንት በይፋ ተከፈተ

ከመጋቢት 15 እስከ 24 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ የሚካሄደው ሀገር አቀፍ የቦንድ ሽያጭ ሣምንት “ጤናችን ይጠበቃል፤ ግድባችን ይጠናቀቃል” በሚል መሪ ቃል መጋቢት 15 ቀን 2012 ዓ.ም. በሃያት ሪጀንሲ ሆቴል በይፋ ተከፍቷል፡፡ ጋዜጣዊ መግለጫም ተሰጥቷል፡፡

 

በመክፈቻው እለት የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ኃይለየሱስ በቀለ፣ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽ/ቤት ዋና ኃላፊ ወ/ሮ ሮማን ገ/ሥላሴ እና እና የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር ፕሬዝዳንትና የጽህፈት ቤቱ አባል ዶ/ር ዮሐንስ በንቲ ተገኝተዋል፡፡

የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ኃይለየሱስ በቀለ ግድቡ የታሰበለትን ዓላማ እንዲያሳካ እና እስኪጠናቀቅ ድረስ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚያደርግ እና ለዚህም በሁሉም ዲስትሪክቶችና ቅርንጫፎች ቦንዱን ለመሸጥ ዝግጅት ማጠናቀቁን ገልጸዋል፡፡

በዚህ መርኃ ግብር 500 ሚሊየን ብር ለማሰባሰብ እቅድ መያዙንም ወ/ሮ ሮማን ገብረ ሥላሴ ገልጸዋል፡፡

ዶ/ር ዮሐንስ በንቲ በበኩላቸው ለግድቡ ፍጻሜ የህብረተሰቡ ድጋፍ ሚናው የጎላ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የቦንድ ሽያጭ ሣምንቱ በይፋ መከፈቱ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ለማነቃቃት የሚረዳ በመሆኑ መገናኛ ብዙኃን በበኩላቸው የተጀመረውን የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከዳር ለማድረስ የኢትዮጵያ ህዝብ የቦንድ ግዥው ላይ ተሳትፎ እንዲያደርጉ በመግለጫው ጥሪ አቅርበዋል፡፡

 

ከዚህ በተጨማሪ ከዚህ በፊት ቦንድ የገዙና የመውሰጃ ጊዜያቸው የደረሰ ካሉም ጊዜውን እንዲያራዝሙ፤ ትላልቅ ድርጅቶችም ከዚህ ቀደም ያደርጉት የነበረውን ልገሳና የቦንድ ግዥ አጠናክረው እንዲቀጥሉ እና በአሁኑ ጊዜም 71% የደረሰውን የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ እንዲጠናቀቅ የበኩላቸውን አስተዋጽዖ እንዲያበረክቱ በመግለጫው ወቅት መልእክት ተላልፏል፡፡