ባንኩ ለኮሮና ቫይረስ ሥርጭት መከላከል 5 ሚሊዮን ብር ለገሰ

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በሃገር አቀፍ ደረጃ የኮሮና ቫይረስ (COVID-19) ሥርጭትን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ብር 5 ሚሊዮን ድጋፍ አደረገ፡፡

 

 

ባንኩ የገንዘብ ድጋፉን ያደረገው መጋቢት 24 ቀን 2012 ዓ.ም. ሠላም ሚኒስቴር በሚገኘው የኮቪድ-19 ብሔራዊ ድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ ጽ/ቤት በአካል በመገኘት ነው፡፡ 

የባንኩ ፕሬዚዳንት ተወካይ እና ም/ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ዋቄ በዚህ ወቅት እንደተናገሩት ይህን ሥርጭት ለመከላከል ከምንጊዜውም በላይ መደጋገፍ ያስፈልጋል፤ ይህ በሽታ ማንን እንደሚያጠቃ አይታወቅም፤ ይህን ድጋፍ ስናደርግ ለራሳችን እና ለምንወዳቸው ጭምር በማሰብ መሆኑን ታሳቢ በማድረግ ከመቼውም ጊዜ በላይ መተጋገዝና እና መረዳዳት ያስፈልጋል ብለዋል፤ በተለይም በኢንቨስትመንት ሥራ ላይ ለተሰማሩ የባንኩ ደንበኞች ሠራተኞቻቸውን በአግባቡ እንዲይዙና እንዲንከባከቡ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡

የኮቪድ-19 ብሔራዊ የድጋፍ አሰባሳቢ ንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢ አምባሳደር ምሥጋኑ አረጋ በበኩላቸው ይህን ፈታኝ ጊዜ እኛው ለእኛው፣ ኢትዮጵያውያን ለኢትዮጵያውያን ሆነን አገርና ዜጋ በማዳን መሻገር ይኖርብናል ያሉ ሲሆን፤ በዚህ አገርንና ዜጋን የማዳን ጥረት የገንዘብ ድጋፍ ላበረከቱ ተቋማት በመንግስት ሥም ምሥጋና አቅርበዋል፡፡

በእለቱ የኢትዮጵያ ልማት ባንክን አስተዋጽዖ ጨምሮ ከተለያዩ ተቋማት ብር 47 ሚሊዮን ለመሰብሰብ እንደተቻለ ታውቋል፡፡