ባንኩ ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ 5 ሚሊዮን ብር በስጦታ አበረከተ

 

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የሚውል ብር 5 ሚሊዮን መጋቢት 25 ቀን 2012 ዓ.ም. በስጦታ አበርክቷል፡፡

 ባንኩ የገንዘብ ስጦታውን ያበረከተው በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽ/ቤት በአካል በመገኘት ነው፡፡

የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ኃይለየሱስ በቀለ የቦንድ ስጦታውን ለጽ/ቤቱ ካስረከቡ በኋላ ባደረጉት ንግግር ባንኩ ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ቦንድ በማቅረብ፣ ሽያጩን በማስተባበር እና በማስተዳደር አስተዋጽዖ እያደረገ እንደሚገኝ፣ ይህንኑ ጉልህ አስተዋጽዖ በማጠናከር በዛሬው እለትም ባንኩ ለግድቡ ግንባታ የሚውል 5 ሚሊዮን ብር በስጦታ ማበርከቱን እና ግንባታው እስኪጠናቀቅ ድረስም አስተዋጽዖው እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡

አቶ ኃይለየሱስ ከዚህ ቀደም መላው የባንኩ ሠራተኛ ሁለት ዙር የቦንድ ግዥ መፈጸሙን አስታውሰው አሁንም ግንባር ቀደም መሪ እና አርአያ በመሆን የባንኩ ማኔጅመንት የቦንድ ግዥ ለመፈጸም መወሰኑን ተናግረው፣ መላው ሠራተኛም ይህንኑ አርአያ እንዲከተል መልእክት አስተላልፈዋል፡፡

በመቀጠል የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽ/ቤት ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሮማን ገብረሥላሴ በበኩላቸው ባንኩ ለግድቡ ግንባታ መጠናቀቅ ላበረከተው የ5 ሚሊዮን ብር የገንዘብ ስጦታ አመስግነው ሌሎች መሰል የፋይናንስ ተቋማትም የባንኩን አርአያ በመከተል ዋናው ጤና ስለሆነ ጤናን በመጠበቅ አስተዋጽዖ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ባንኩ ለግድቡ ግንባታ ካበረከተው አስተዋጽዖ በተጨማሪ የኮሮና ቫይረስ ሥርጭት በአገራችን እንዳይስፋፋ በሃገር አቀፍ ደረጃ ለሚደረገው ጥረት የ5 ሚሊዮን ብር ልገሳ ማድረጉ ይታወቃል፡፡