ስድስተኛው ዙር የቦንድ ሳምንት ተጀመረ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 20፣ 2014 (የኢትዮጵያ ልማት ባንክ)
የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ስድስተኛው ዙር የቦንድ ሽያጭ ሳምንት ትናንት በኢሊሌ ሆቴል በተዘጋጀ ሥነ ሥርዓት ተጀመረ፡፡
የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ 11ኛ ዓመትን አስመልክቶ የተዘጋጀውን ስድስተኛውን ዙር የቦንድ ሳምንት፤ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና የግድቡ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት በጋራ አዘጋጅተዋል፡፡ የቦንድ ሳምንቱ ለ15 ቀናት የሚቆይ ነው፡፡
በዚሁ ማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓት ላይ የኃይል ማመንጨት ሥራውን በስኬት የጀመረው የሕዳሴው ግድብ ሙሉ ግንባታውን ከፍጻሜ ለማድረስ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ቦንድ በመግዛት የሚያደርገውን ተሳትፎ እንዲያጠናክር የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ጥሪ አቅርቧል፡፡
ባንኩ ስፖንሰር ያደረገው ከወለድ ነጻ የባንክ እና የኢንሹራንስ አገልግሎት መድረክ ተካሄደ
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በዋና አጋርነት ስፖንሰር በማድረግ የተሳተፈበት ከወለድ ነጻ የባንክ እና የኢንሹራንስ አገልግሎት ላይ ያተኮረ መድረክ መጋቢት 7 ቀን 2014 ዓ.ም በሸራተን አዲስ ተካሂዷል፡፡
በመድረኩ ላይ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የኢትዮጵያ የአካውንቲንግ እና ኦዲቲንግ ቦርድ ዳይሬክተር ጄኔራል፣ የግል ባንክ እና ኢንሹራንስ ተወካዎች፣ ባለድርሻ አካላት እና አማካሪ ድርጅቶች ተገኝተዋል፡፡
ባንኩን በመወከል መድረኩ ላይ የተገኙት ም/ፕሬዚዳንት- ኮርፖሬት አገልግሎት አቶ ሰፊዓለም ሊበን መልእክት አስተላልፈዋል፡፡ በመልእክታቸው የኢትዮዽያ ልማት ባንክ የሸሪአ መርሆዎችን የተከተለ ከወለድ ነጻ የሆነ የትላልቅ ፕሮጀክትና የሊዝ የፋይናንስ አገልግሎት ለመስጠት ተገቢውን ጥናት አስጠንቶ አገልግሎቱን ባስቀመጣቸው ስትራቴጂዎች በቅርቡ እውን ለማድረግ የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን በማጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
ባንኩ በሌሎች ባንኮች ሊሸፈኑ የማይችሉ የፋይናንስ አገልግሎቶችን በማቅረብና የሀገሪቱን የማክሮ ኢኮኖሚ ክፍተት በመሙላት በሀገራዊ እድገት ላይ የራሱን ሚና በመጫወት እንደሚገኝ በመግለጽ አገልግሎቱን ከሚሹ ሁሉም ደንበኞቹ ጋር በጋራ ለመስራት ባለው ጠንካራ ፍላጎት የተነሳ የረጅም ጊዜ ብድር ወስደው በልማት ስራ ላይ በማዋል ራሳቸውንና ሀገራቸውን እንዲያሳድጉ ም/ፕሬዚዳንቱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በቀጣይነትም ባንኩ ሀገራዊ እድገት ላይ አስተዋጽኦ ያላቸውን የግንዛቤ መፍጠሪያ መሰል መድረኮችን ለመደገፍ የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥል አክለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ሰራተኞች የሴቶች ቀን /March 8/ አከበሩ
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ሰራተኞች በሀገር አቀፍ ደረጃ ለ46ተኛ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ111ኛ ጊዜ የሚከበረውን ዓለም አቀፉን የሴቶች ቀን /March 8/ መጋቢት 29 ቀን 2014ዓ.ም በባንኩ የመሰብሰቢያ አዳራሽ አክብረዋል፡፡
“እኔ የእህቴ ጠባቂ ነኝ” እና “የስርዓተ ፆታ እኩልነት ለዘላቂ ልማት” በሚሉ መሪቃሎች በተከበረው በዓል ላይ የባንኩ ከፍተኛ አመራሮች፣ የኢትዮጵያ ሰራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽ የሴቶች ጉዳይ መምሪያ ሃላፊ ወ/ሮ ራሄል አየለ፣ የኢትዮጵያ ፋይናንስ ተቋማት ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ደስታ በርሄ እንዲሁም የባንኩ ሴት አመራሮችና ሰራተኞች ተገኝተዋል፡፡
በፕሮግራሙ ላይ የባንኩን ፕሬዝዳንት በመወከል የተገኙት የኮርፖሬት አገልግሎት ም/ፕ አቶ ሰፊዓለም ሊበን የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት ያስተላለፉ ሲሆን፤ በመልእክታቸውም በማህበረሰባችን ውስጥ ተደራራቢ ሃላፊነትን በመወጣት ከፍተኛ አስተዋፅኦ በማድረግ ትልቁን ቁጥር የሚይዙት ሴቶች መሆናቸውን ገልፀው እንደ ተቋምም እንደ ማህበረሰብም ሴቶችን ማገዝና መደገፍ ውጤታማ ስራ ለመስራት መሰረት እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡ አክለውም ሴቶችን ለማብቃት እና የባንኩን የሴት አመራሮች ቁጥር ለመጨመር እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሰራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽ የሴቶች ጉዳይ መምሪያ ሃላፊ ወ/ሮ ራሄል አየለ በበኩላቸው ባስተላለፉት መልእክት ሴቶች እድሉ ከተሰጣቸውና ራሳቸውን እንዲያበቁ እገዛ ቢደረግላቸው ከፍተኛ ለውጥ ማምጣት የሚያስችል እምቅ ሃይልና ችሎታ ባለቤት ናቸው ያሉ ሲሆን፤ ባንኩ ሴቶችን ወደ አመራር ቦታ ለማምጣት ትኩረት ሰጥቶ አንዲሰራ ጠይቀዋል፡፡ አያይዘውም “እኔ የእህቴ ጠባቂ ነኝ” በሚለው መርህ መሰረት ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በተለይም ወንድ ሰራተኞች የሴቶችን ጥቃል ለመከላከል ዘብ እንዲቆሙ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በፕሮግራሙ ማጠቃለያ ላይ ሀገራችን በገጠማት የህልውና ማስከበር ጦርነት ወቅት ሃገራቸውን እና ወገናቸውን ከጥቃት ለመታደግ የህይወት መሰዋዕትነት ለመክፈል በመቁረጥ በፍቃደኝነት ለዘመቱ የባንኩ ሰራተኞች የእውቅና አሰጣጥ ስነስርዓት ተካሂዷል፡፡
ባንኩ ከማዕድን ሚኒስቴር ጋር ውይይት አደረገ
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ከማዕድን ሚኒስቴር ጋር በትብብር መሥራት በሚችልባቸው አስቻይ ሁኔታዎች ዙሪያ ጥር 26 ቀን 2014 ዓ.ም በባንኩ ዋናው መሥሪያ ቤት ውይይት አድርጓል፡፡
በውይይቱ ላይ የባንኩ ፕሬዚዳንት የተከበሩ ዶ/ር ዮሐንስ አያሌው /ፒ.ኤች.ዲ/ እና ምክትል ፕሬዚዳንቶች፣ ከማዕድን ሚኒስቴር በኩል ደግሞ የተከበሩ አቶ ታከለ ኡማ እና ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡
የባንኩ ፕሬዚዳንት የተከበሩ ዶ/ር ዮሐንስ አያሌው (ፒ.ኤች.ዲ) ስለባንኩ ፖሊሲዎችና አሰራሮች፣ እንዲሁም ብድር ስለሚሰጥባቸው መስፈርቶች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ ከብድር ሥራ ጎን ለጎን በስልጠና እና በትብብር /partnership/ መሥራት ስለሚቻልባቸው አስቻይ ሁኔታዎች ገለጻ አድርገዋል፡፡
የማዕድን ሚኒስትሩ በተደረገላቸው ገለጻ አመስግነው በቀጣይ በማዕድን ልማት ዘርፍ ከባንኩ ጋር በትብብር በመሥራት በአገር ኢኮኖሚ እድገት ላይ ለውጥ ለማምጣት እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡
Page 8 of 28