ባንኩ ዓመታዊ በዓሉን በድምቀት አከበረ
“ባንካችንን ወደ ዓለምአቀፍ ደረጃ እናሳድገዋለን!” ክቡር ዮሐንስ አያሌው (ፒ.ኤች.ዲ)
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ዓመታዊ በዓሉን ሐምሌ 24 ቀን 2013 ዓ.ም በአዲስ አበባ ግራንድ ኤሊያና ሆቴል አዳራሽ በድምቀት አከበረ፡፡
በባንኩ ዓመታዊ በዓል ላይ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የባንኩ ፕሬዚዳንት ክቡር ዮሐንስ አያሌው (ፒ.ኤች.ዲ) “የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በተለያዩ ምክንያቶች በተፈጠሩ ክፍተቶች ገብቶ ከነበረበት ‘የይቀጥላል ወይም አይቀጥልም’ መስቀለኛ መንገድ ወጥቶ ቀጣይነቱን ከማረጋገጥም ባሻገር ታሪካዊ የሚባል ትርፍ በማትረፍ እና የተበላሸ ብድሩን በመቀነስ የተጀመረው የትራንስፎርሜሽን ሂደት እየቀጠለ ባለበት ሁኔታ የባንኩን ዓመታዊ በዓል ለማክበር በመቻላችን እንኳን ደስ ያለን” የሚል የደስታ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
ክቡር ፕሬዚዳንቱ ባንኩን እንዲመሩ ከተመደቡበት ቀንና ሰዓት ጀምሮ ባንኩን በሁለንተናዊ መልኩ ለማሻሻል ባደረጉት ጥረትና በወሰዷቸው ስትራቲጂያዊ እርምጃዎች ሁሉ በየደረጃው ያሉ የባንኩ ሥራ አመራሮችና ፈጻሚዎች አብረዋቸው ለለውጡ ባይደክሙ ኖሮ ይህን ውጤት ማስመዝገብ የማይታሰብ መሆኑን ጠቅሰው ለሁሉም በድርሻው ልክ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በዚህ ዓመት የተመዘገበው አፈጻጸም ባንኩን እንደ ተቋም፣ ኃላፊዎችን እንደ አመራር እና መላውን የባንኩን ሠራተኛ እንደ ፈጻሚ አንገትን በኩራት ቀና አድርገን እንድንጓዝ የሚያስችልና በሀገር የብልፅግና ጉዞ ምዕራፍ ላይ በበጎ አሻራ አድራጊነት ታሪክን በጉልህ ቀለም የሚያጽፍ የሁሉም የጋራ የድካም ውጤት መሆኑን የገለጹት ክቡር ዮሐንስ አያሌው (ፒ.ኤች.ዲ) አንድን በመቀጠልና ባለመቀጠል መካከል መስቀለኛ መንገድ ላይ የነበረን ተቋም ከውድቀት አድኖ ቀጣይነቱን ከማረጋገጥም ባለፈ ትርፋማ ማድረግ መቻል ተገቢው ዕውቅና ሊሰጠው ይገባል፤ ይሰጠዋልም ብለዋል፡፡
የባንኩን የአመሠራረት ታሪክና የተጓዘባቸውን የስኬት ዘመናት በንግግራቸው ያስታወሱት ፕሬዚዳንቱ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ እጅግ የተከበረ ስምና ዝና ያለው እንዲሁም ብዙ ሊነገርለት የሚገባ አኩሪ ታሪክን ያቀፈ አንጋፋ ባንክ መሆኑ “በእጅ የያዙት ወርቅ” ሆኖብን “እንደ መዳብ” ካልቆጠርነው በቀር የኢትዮጵያ ልማት ባንክ አመራርም ሆነ ሠራተኛ መሆን ከታሪኩ ታሪክን፣ ከክብሩም ክብርን ለመካፈል የሚያስችል ዕድለኝነት ስለሆነ ሁላችንም ባንኩን በሚመጥን ቁመና ላይ መገኘት አለብን ሲሉ በአጽንዖት አሳስበዋል፡፡
የባንኩን ዓመታዊ የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ያቀረቡትና የቀጣይ ዓመቱን ዕቅድ ያስተዋወቁት ክቡር ፕሬዝዳንቱ ባንኩ ከነበረበት ችግር ተላቆ ትርፋማ መሆን መጀመሩና ቀጣይነቱን ማረጋገጡ እንደተጠበቀ ሆኖ “የኢትዮጵያ ልማት ባንክን ወደ ዓለምአቀፍ ደረጃ ለማሳደግ እንሠራለን” ብለዋል፡፡
ባንኩ የጀመረውን ለውጥ ከግብ ለማድረስም የመዋቅርና አደረጃጀት ለውጥ ተሠርቶ በመጠናቀቅ ላይ ስለሆነ በባንኩ ታሪክ ትልቅ ሽግግርን በመፍጠር ለሀገራዊ ብልፅግና ጉልህ ሚና የሚጫወትበት መንግድ መጀመሩን አብስረዋል፡፡
ከሠራተኞች ማኅበር ፕሬዚዳንትና ከሌሎችም የበዓሉ ታዳሚዎች ከደመወዝ ጉርሻ/ቦነስ/፣ እርከን ጭማሪ፣ ከመዋቅራዊ ለውጥና የሰው ኃይል አመዳደብ ጋር የተያያዙ ጥያቄዎች ተነስተው ማብራያ ተሰጥቶባቸዋል፡፡ ከሠራተኛ ጥቅማጥቅም ጋር በተያያዘ በዚህ ዓመት ባንኩ ትርፋማ በመሆኑ /ብር 3.3 ቢሊዮን የተጣራ ትርፍ በማስመዝገቡ/ ጉርሻም ሆነ የእርከን ጭማሪ ለመፍቀድ ውይይት መጀመሩ እንዲሁም ከመዋቅር ለውጥ ጋር ተያይዞ የሚደረገው ምደባም በሙያና በሥራ ልምድ ተመዝኖ ግልጽነት በሰፈነበት አሠራር ብቻ እንደሚፈጸም ገልጸዋል፡፡
በመጨረሻም በሀገራዊ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ የተለያዩ ሥነ ጽሑፎች ቀርበው፣ ውይይት ተደርጎ ኢትዮጵያ ትቀጥል ዘንድ የባንኩ ሠራተኞች የአንድ ወር የተጣራ ደመወዝ በአንድ ዓመት ተከፍሎ የሚያልቅ ድጋፍ እንዲደረግ ተወስኗል፡፡ የባንኩ ሠራተኛ ማኅበር ለባንኩ ከፍተኛ ውጤት መመዝገብ ትልቁን ድርሻ በመያዛቸው የባንኩን ፕሬዚዳንት ሸልሟል፤ የኬክ ቆረሳ መርኃ ግብርም ተካሂዷል፡፡
የባንኩ ሠራተኛ ማኅበር 42ኛ መደበኛ ስብሰባውን አካሄደ
"ሠራተኛው በማኔጅመንቱ እንዲተማመን እንፈልጋለን" - አቶ ሰፊዓለም ሊበን
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ መሠረታዊ ሠራተኛ ማኅበር ሐምሌ 15 ቀን 2013 ዓ.ም 42ኛ መደበኛ የምክር ቤት ስብሰባውን በባንኩ ዋና መስሪያ ቤት አዳራሽ አካሂዷል፡፡
በማኅበሩ መደበኛ ስብሰባ ላይ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የባንኩ ምክትል ፕሬዝዳንት-ኮርፖሬት አገልግሎት አቶ ሰፊዓለም ሊበን ናቸው፡፡
“የሠራተኛውን መብት ማስጠበቅ ለተቋሙ ሕልውና ወሳኝ ነው፣ የሠራተኛውን መብት ለማስጠበቅ ደግሞ በማኅበር መደራጀት አስፈላጊ ነው” ያሉት አቶ ሰፊዓለም በአሁኑ ሰዓት የባንኩ ከፍተኛ ማኔጅመንት መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣትና ውጤታማ ጉዞን ለማስቀጠል ቆርጦ በመነሳት ሌት ተቀን እየሠራና አበረታች ትርፍም እያስመዘገበ መሆኑን ጠቁመው “ሠራተኛው በማኔጅመንቱ እንዲተማመን እንፈልጋለን፣ ተደራጅቶ እስካገዘንና ባንኩ በውጤታማነት እስከቀጠለ ድረስ በሂደት እየተጠና የማይከበርለት መብትና የማይመለስለት ጥያቄ አይኖርም” ብለዋል፡፡
በተለይም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የሠራተኛ ማኅበሩ ሥራ አስፈጻሚዎችና የባንኩ ከፍተኛ አመራሮች የበለጠ ተቀራርበው መሥራት በመጀመራቸው የሠራተኛው ፍላጎት በተሻለ መልኩ መመለስ መጀመሩና ባንኩም በውጤታማነት ቀጣይነቱን ማረጋገጡ ትልቅ ትርጉም የሚሰጠው ነው ብለዋል ምክትል ፕሬዚዳንቱ፡፡
ባንኩ በዚህ ዓመት ውጤታማ የሆነው ከፍተኛ አመራሩ የወሰዳቸውን ስትራቴጂካዊ ውሳኔዎች ሠራተኛው ደግፎ ለለውጥ ስለተንቀሳቀሰ መሆኑን ተናግረው ለወደፊቱም ለተሻለ ውጤት እንደሚረባረብ ያላቸውን ጽኑ እምነት ገልጸዋል፡፡
የሠራተኛ ማበህሩ ሊቀመንበር አቶ ይበልጣል ያየህ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ባንካችን ላስመዘገበው የላቀ ውጤት የእንኳን ደስ አላችሁ መልክት ካስተላለፉ በኋላ ለዚህ ውጤት መመዝገብ ከፍተኛውን ሚና ለተጫወቱ የባንኩ ከፍተኛ የማኔጅመንት አባላት በሠራተኛው ስም ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ ውጤቱ የተመዘገበው ከባንኩ ከፍተኛ የስራ አመራር አባላት ጠንክራ ሥራ በተጨማሪ የባንኩ ሰራተኞችም የተሰጣቸውን ኃላፊነት በሚገባ በመወጣታቸው ጭምር በመሆኑ የባንኩ ሰራተኞችም ምስጋና እንደሚገባቸው ገልፀዋል፡፡
በዚህ 42ኛው የምክር ቤት ጉባዔም የሠራተኛ ተወካዮች በሆኑ የምክር ቤት አባላት መነሳት የሚገባው ጉዳይ ባንኩ ባስመዘገበው ውጤት በመበረታታት የባንኩን ዘላቂ ውጤታማነት ለማምጣት ከፊት መቆም እንደሚጠበቅ መገንዘብ እንደሚገባ አንስተዋል፡፡ ምክንቱም እንደ ሠራተኛ ማኅበር ተወካይነታችን የሠራተኛው ጥቅም እንዲከበር የምንፈልግ ከሆነ የባንካችንን ውጤታማነት ማረጋገጥ አስፈላጊ በመሆኑ ሁሉም ሠራተኛ በትጋት መስራት ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡
ባንኩ ውጤታማ እሰከሆነ ድረስ ደግሞ የሠራተኛው ጥቅምና መብት እንዲከበር ማህበሩ ጠንክሮ እንደሚሰራና የባንኩ የበላይ አመራርም ተመሳሳይ አቋም እንዳለው፣ ለዚህም ቃል እደተገባላቸው አውስተዋል፡፡ ከዚህ በፊት በሠራተኛው በተደጋጋሚ የሚቀርቡ ጥያቄዎችን በተመለከተ ማህበሩ ለባንኩ ማኔጅመንት በጽሑፍና በቃል በማቅረብ የውሳኔ ሐሳብ እየተጠባበቀ እንደሚገኝ አስታውሰው የባንኩ የሪፎርም እና ሪስትራክቸሪንግ ስራዎች እንደተጠናቀቁ የባንኩ ከፍተኛ ስራ አመራር ሠራተኛውን የሚጠቅም መልስ እንደሚሰጡ ሙሉ ተስፋ እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ፋይናንስ ተቋማት ኢንዱስትሪ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ደስታ በርሔ በበኩላቸው ባንኩ ያስመዘገበው ለውጥ ሁላችንም ከገመትነው በላይ ነው፡፡ ይህም የባንኩን አመራርና የሠራተኛውን ተግባብቶ መሥራት የሚያመለክት ነው፡፡ በመሆኑም ይህን ለውጥ በብቃት ለመሩትና ቃላቸውን በተግባር ለተረጎሙት የባንኩ ከፍተኛ አመራሮች አድናቆትና ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ከባንኩ ዲስትሪክት ጽ/ቤቶች ሠራተኛውን ወክለው ስብሰባውን የታደሙት ተወያዮችም ለምክትል ፕሬዚዳንቱ በርካታ ጥያቄዎችን አንስተው ማብራሪያ ተሰጥቷቸዋል፡፡ እነዚህም፡- በቤት ብድር መመሪያ ዙሪያ፣ በአበል አከፋፈል፣ ደመወዝና የደረጃ እድገት ፣ዝውውር፣ በበረሃማ አካባቢ የሚሠሩ ሠራተኞች ጥቅማጥቅምና የቦታ ለውጥ፣ ከቤተሰብ ሕክምና፣ ወዘተ፣ ጋር የተያያዙ ጥያቄዎች ተነስተው ውይይት ተደርጎባቸዋል፤ ምላሽም ተሰጥቶባቸዋል፡፡
ከሠራተኛ ተወካዮች ለተነሱ ሐሳቦች ማብራሪያ የሰጡት አቶ ሰፊዓለም ሁሉም ጥያቄዎች ትክክለኛና መልስ የሚፈልጉ መሆናቸውን አስምረውበት ሆኖም ሁሉም በአንድ ጊዜ ሊመለስ ስለማይችል የተጀመሩ መልካም መሻሻሎችን እውቅና በመስጠት ላልተመለሱት በጋራ መሥራት ይገባል ብለዋል፡፡ የሠራተኛው መብት በዘላቂነት እንዲከበርና ጥቅማጥቅሙ እንዲጠበቅለት ከተፈለገ አብዛኞቹ ጥያቄዎች በጥናት መመለስ እንዳለባቸው አስረድተዋል፡፡ መመሪያ ሲወጣም ሆነ አሠራር ሲዘረጋ የባንኩ ዋና አላማ ሠራተኛውን ተጠቃሚ ማደረግና ለውጤታማነት ማነሳሳት እንጅ ሌላ ስላልሆን የሠራተኛውን ችግር የማይፈቱና ለተጨማሪ ቅሬታ በር የሚከፍቱ መመሪያዎችና አሠራሮችም ተለይተው የማይሻሻሉበት ምንም ምክንያት የለም ብለዋል፡፡
የሠራተኛ ማኅበሩ 42ኛ መደበኛ የምክር ቤት ስብሰባ አንዳንድ የፕሮቶኮል ውሳኔዎችን በማሳለፍና እና የቀድሞ የማኅበሩ አመራሮችን በክብር በመሸኘት ተጠናቋል፡፡
የባንኩ ሠራተኞች በችግኝ ተከላ መርኃ ግብር ላይ ተሳተፉ
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ “ኢትዮጵያን እናልብሳት” በሚል መርህ እየተካሄደ በሚገኘው ሀገር አቀፍ የችግኝ ተከላ መርኃ ግብር ላይ ሐምሌ 10 ቀን 2013 ዓ.ም ተሳትፎ አድርጓል፡፡
የባንኩ የበላይ አመራር፣ የሥራ መሪዎችና ሰራተኞች ባንኩ ከዚህ ቀደም ባለማው ጉለሌ ክፍለ ከተማ በሚገኘው የእጽዋት ማዕከል በአካል በመገኘት፣ በባንኩ ውስጥና ዙሪያ ችግኞችንና የቤት ውስጥ የማስዋቢያ እጽዋት በመትከል ተሳትፎ አድርገዋል፡፡ እንዲሁ የጉለሌ ክፍለ ከተማ ሥራ አስፈጻሚዎችና ነዋሪዎች በችግኝ ተከላ መርኃ ግብሩ ላይ ተሳትፈዋል፡፡
የባንኩ ፕሬዚዳንት ክቡር ዮሐንስ አያሌው (ፒ.ኤች.ዲ) ባንኩ ባለማው እጽዋት ማእከል የችግኝ ተከላው መርኃ ግብር ከመካሄዱ አስቀድሞ የመክፈቻ ንግግር አድርገዋል፡፡ በንግግራቸው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በልዩ ሁኔታ ለአረንጓዴ አሻራ ትኩረት በመስጠት በጉለሌ እፅዋት ማዕከል አካባቢ ቦታ በመረከብ ከብር 15 ሚሊዮን በላይ ወጪ አድርጎ ያለማው ውብ የባንኩ አረንጓዴ መናፈሻ ፓርክ ኢትዮጵያን በማልበስ ሂደት ውስጥ ያለንን መልካም ጅምርና ቁርጠኝነት ያሳያል ብለዋል፡፡
ባንኩ በዛሬው ዕለት ከጉለሌና ቂርቆስ ክፍለ ከተሞች ጋር በመተባበር በዋናው መስሪያ ቤት ግቢና ቀደም ብሎ ባንኩ ባለማው የጉለሌ እፅዋት ማዕከል ውስጥ 3,675 ችግኞችንና የግቢ ማስዋብ እፅዋቶች፣ እንዲሁም በባንኩ የዲስትሪክት ጽ/ቤቶች አማካይነት ከ18,000 ችግኞች በመተከል ላይ ተተክለዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ባንኩ ለችግኝ ግዥ እና ሌሎች ተያያዥ ወጪዎች ለጉለሌና ቂርቆስ ክፍለ ከተሞች የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉን እንዲሁ ገልጸዋል፡፡
የጉለሌ ክፍለ ከተማ አስተዳደር የብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ የተከበሩ አቶ ሲሳይ እንዳለ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ሀገራዊ ጥሪውን መሰረት በማድረግ አረንጓዴ አሻራውን ለማኖር ክፍለ ከተማውን መርጦ ተሳትፎ በማድረጉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
ባንኩ ይህንን ሀገራዊ የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ከመደገፍ አኳያ ለቂርቆስና ጉለሌ ክፍለ ከተሞች ለችግኝ ተከላ መርኃ ግብር እንዲሆናቸው የፋይናንስ እገዛ ከማድረጉ በተጨማሪ ለገጽታ ግንባታ ይሆነው ዘንድ የባንኩን ስምና ዓርማ የያዙ የማስተዋወቂያ ቁሳቁሶችን ማለትም ኮፍያ እና ሳኒታይዘር እስክሪብቶዎችን አሰራጭቷል፡፡
የባንኩ ዓመታዊ የሥራ አፈጻጸም ምክክር መድረክ ተካሄደ
በባንኩ የ2013 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት እና የቀጣይ ዓመት የትኩረት አቅጣጫ እንዲሁም በባንኩ የለውጥ ሥራዎች ትግበራ የባለድርሻ አካላት ድጋፍ ዙሪያ በአዳማ ከተማ የምክክር መድረክ ተካሂዷል፡፡
የምክክር መድረኩ የተካሄደው ሐምሌ 03 ቀን 2013 ዓ.ም ሲሆን የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የገቢ፣ በጀትና ፋይናንስ እና የንግድና ኢንዱስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴዎች እንዲሁም የመንግስት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የባንኩ ፕሬዚዳንትና ም/ፕሬዚዳንቶች እንዲሁም ሌሎች የሥራ መሪዎች ተሳትፈዋል፡፡
የምክክር መድረኩን በንግግር የከፈቱት የባንኩ ፕሬዚዳንት የተከበሩ ዮሐንስ አያሌው /ፒ.ኤች.ዲ/ ባንኩ እንደ ፖሊሲ ባንክ ከተቋቋመበት ከ1901 ዓ.ም ጀምሮ ከአንድ ምዕተ ዓመት በላይ ሀገራዊ የኢኮኖሚ ሽግግርን በሚፈጥሩ የልማት ዘርፎች ላይ የተመሠረቱና በመላ ሀገሪቱ የተዘረጉ ፕሮጀክቶችን እየደገፈ በርካታ ስኬታማ ልማታዊ ለውጦችን እያስመዘገበ የመጣ ባለ ታሪክና ባለ መልካም አሻራ ባንክ ነው ብለዋል፡፡
ሆኖም ባለፉት አስር ዓመታት የመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ትግበራን ተከትሎ በነበሩ ውጫዊ እና ውስጣዊ ጫናዎች ምክንያት ባንኩ የሰጠውን ብድር ማስመለስ ተስኖት የተበላሹ ብድሮቹ ከፍተኛ ደረጃ ላይ በመድረሱ ቀጣይነቱ ላይ ጥያቄ ሆኖ ቆይቷል፡፡
በዚህ አጣብቂኝ ውስጥ መንግስት በባንኩ ቀጣይነት ላይ ከመጠራጠር ይልቅ አመራሩን እና አሠራሩን በማሻሻል በውጤታማነት ለማስቀጠል ወስኖ ታላቅ ኃላፊነት ጋራ አዳዲስ አመራሮችን ስለመመደቡም ተናግረዋል፡፡ በዚህም የቢዝነስ ሞዴል ጥናት፣ የባንኩ የገንዘብ ምንጭ ጥናት ይህንን ተከትሎም የባንኩ መዋቅራዊ አደረጃጀት ላይ ለውጦች እየተደረጉ ስለመሆናቸውም ጠቁመዋል፡፡
በማከልም በተጠናቀቀው የ2013 በጀት ዓመት ባንኩ የተበላሸ የብድር ምጣኔውን ከ34 በመቶ ወደ 26 በመቶ መቀነስ እንደቻለና ዓመታዊ የተጣራ ትርፉን ወደ ብር 3.2 ቢሊዮን ማሳደጉን ገልጸዋል፡፡
በመቀጠል የመንግስት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ትዕግስቱ አምሳሉ በበኩላቸው ባንኩ ትልቅ አሻራ ያለው ባንክ መሆኑን በመጥቀስ አጋጥሞት የነበረውን ችግር በአጭር ጊዜ ውስጥ በመሻገር ለውጤት መብቃቱ የሚደነቅ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በአጭር ጊዜ ውስጥ ለተመዘገበው ውጤትም የኤጀንሲው፣ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የገቢ፣ በጀትና ፋይናንስ ቋሚ ኮሜቴ አባላት እና ሌሎች የመንግስት አካላት ያደረጉት ድጋፍና ክትትል የጎላ ሚና እንደነበረው ጠቅሰዋል፡፡ ባንኩ የጀመረው የለውጥ ሂደት ከዚህም በላይ ሰፍቶ የተሻለ ውጤት እንዲያመጣ የተጀመረውን የአሠራር፣ የአደረጃጀት እና የአማራር ሪፎርም አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አሳስቧል፡፡ ለዚህም ኤጀንሲው የሚያደርገው ድጋፍና ክትትል ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ቃል ገብተዋል፡፡
እንዲሁም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የገቢ፣ በጀትና ፋይናንስ ቋሚ ኮሜቴ ሰብሳቢ ተወካይ ቋሚ ኮሚቴው ምንም እንኳ የባንኩ አጠራጣሪ ብድር ከፍተኛ ቢሆንም ባንኩ የጀመረው የሪፎርም ሥራ ውጤት እንደሚያመጣ በማመን ባንኩ ያቃረበውን የካፒታል ጭማሪ ጥያቄ በመንግስት ይሁንታ እንዲያገኝ በቋሚ ኮሚቴው ጥረት ሲደረግ እንደነበር ገልጸው በተለይም ባንኩ ከነ እዳቸው የተረከባቸውን ትላልቅ ፕሮጀክቶች የግብር እዳቸው በመንግስት እንዲሰረዝ ከፍተኛ ሥራ ሲሰራ እንደነበር ጨምረው አብራርተዋል፡፡
የመድረኩ ተሳታፊ የነበሩት የምክር ቤት አባላት በሰጡት አስተያየት ባንኩ የጀመራቸው የለውጥ ሥራዎች እንዳይቀለበሱ የባንኩ የሥራ አመራር ቦርድ እንዲሁም ባለድርሻ አካላት ለባንኩ የተጠናከረ ድጋፍ መስጠት እንዳለባቸው በአንክሮ አሳስበዋል፡፡
በመጨረሻም ባንኩ አሁን ለሚገኝበት ውጤት እንዲበቃ ጉልህ አስተዋጽዖ ላደረጉ ተቋማት የምስጋና ምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል፡፡
Page 10 of 26