ታላቅ የምስራች በአነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ ስራ ላይ ለተሰማራችሁ እና ለወደፊቱ እቅዱ ላላችሁ የቀረበ የሥልጠና ማስታወቂያ ጥሪ
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የመንግስትን የትኩረት አቅጣጫ መሠረት በማድረግ በማኑፋክቸሪንግ፣ በአግሮ ፕሮሰሲንግ፣ በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ፣ በማዕድን ልማት፣ በቱሪዝም ኢንዱስትሪ፣ በእርሻ እና በአግሪካልቸራል መካናይዜሽን አገልግሎት የሥራ ዘርፎች ለተሰማሩ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የሊዝ ፋይናንሲንግ አገልግሎት /የማምረቻ መሣሪያ አቅርቦት በስፋት ሲሰጥ መቆየቱ ይታወቃል፡፡
ባንኩ አሰራሩን በአዲስ መልክ በማዘመን እና ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት በመስጠት አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ሀገሪቱ ከግብርና መር ኢኮኖሚ ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለምታደርገው መዋቅራዊ ሽግግር የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ በመሆኑ ኢንተርፕራይዞች የበለጠ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እና የሚሰሩትን ሥራ በዕውቀት ላይ የተመሰረተ ለማድረግ ባንኩ በቢዝነስ ፕላን ዝግጅት እና ርዕይ ቀረጻ፣ የፋይናንሽያል ዝግጅትና ትንተና፣ የቢዝነስ አስተዳደር፣ የሰው ኃብት አመራር፣ የገበያ ጥናት፣ የፖሊሲ ቅኝት እንዲሁም የሊዝ ፋይናንሲንግ አሰራር የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ከዚህ ቀደም በስምንት ማዕከላት ማለትም በአዲስ አበባ፣ ባህር ዳር፣ ጂግጂጋ፣ ደሴ፣ ጂማ፣ አዳማ፣ ወላይታ ሶዶ እና ቡታጅራ ከተሞች ላይ መሰጠቱ ይታወሳል፡፡ አሁንም ይህንኑ በማስቀጠል በትግራይ መቀሌ ማእከል ስልጠናውን ለመስጠት ባንኩ በዝግጅት ላይ ይገኛል፡፡
ሥልጠናውን እንዲወስዱ የታሰቡ ተሳታፊዎች 1ኛ) ከባንኩ የፕሮጀክትና የሊዝ ፋይናንሲንግ አገልግሎት እያገኙ ያሉና በሥራ ላይ የሚገኙ ኢንተርፕራይዞች 2ኛ) ለመሳተፍ ቢዝነስ ፕላን ለባንኩ ያቀረቡ ወይም ለማቅረብ የተዘጋጁ 3ኛ) እውቀቱ፣ ሙያው እና አቅሙ ያላቸው ቢዝነስ ፕላን ለማዘጋጀት የሚፈልጉ እና ዝቅተኛውን መስፈርት አሟልተው የባንኩን ድጋፍ የሚፈልጉ አዲስ ኢንተርፕራይዞችንም ጭምር ይመለከታል፡፡
የሊዝ ፋይናንሲንግ አገልግሎት ከባንኩ ለማግኘት በቅድሚያ ባንኩ ያዘጋጀውን ይህንን ሥልጠና መውሰድ ባንኩ ለሚሰጠው አገልግሎት እንደ ቅድመ ሁኔታ የሚወሰድ መሆኑ ታውቆ በኢትዮጵያ ልማት ባንክ መቀሌ ዲስትሪክት ጽ/ቤት እና በስሩ በሚገኙ ቅርንጫፎች በመገኘት እንድትመዘገቡ እና ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት ሥልጠናውን በአግባቡ እንድትከታተሉ ባንኩ በአክብሮት ይጋብዛል፡፡
ሥልጠናው የሚመለከተው የድርጅቱ ባለቤት ወይም ዋና ሥራ አስኪያጅ ወይም ከድርጅቱ የውክልና ደብዳቤ የሚያቀርብ ሲሆን ሃሳብ እና ፍላጎቱ ብቻ ያላቸው ማሳሰቢያው አይመለከታቸውም፡፡
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ፣ የልማት አጋርዎ!!
የባንኩ ሰራተኞች ድምጻቸውን አሰሙ
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ሰራተኞች “ብሔራዊ ክብር በሕብር” በሚል በሀገራችን ላይ የሚደረግ ማንኛውንም ዓይነት የውጭ ጣልቃ ገብነትን በመቃወም ግንቦት 13 ቀን 2013 ዓ.ም ከቀኑ 10፡00-11፡00 በዋናው መ/ቤት ፊት ለፊት በመገኘት ድምጻቸውን አሰምተዋል፡፡
በእለቱም፡-
- "የውጭ ኃይሎች እጃችሁን ከኢትዮጵያ ላይ እንድታነሱ እንጠይቃለን!"
- "ግድቡ የእኔ ነው!"
- :በሀገራችን ላይ የሚደረግ ማንኛውንም ዓይነት ጣልቃ ገብነትና ጫናን አንቀበልም!"
- "በሀገራችን የተጀመረውን ልማት እንደግፋለን!”
የሚሉ መፈክሮችን አሰምተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ለአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ሲሰጥ የቆየው ሃገር አቀፍ ስልጠና ተጠናቀቀ፡፡
በኢትዮጵያ ልማት ባንክ አዘጋጅነት ከመጋቢት 13 - 17 ቀን 2013 ዓ.ም አዲስ በአበባን ጨምሮ በተለያዩ ክልሎች/ማዕከላት ሲሰጥ የቆየው ስልጠና አርብ የካቲት 17 ቀን 2013 ዓ.ም ተጠናቋል፡፡
በስልጠናው ማጠቃለያ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡ ሰልጣኞች እንደተናገሩት ስልጠናው በጣም ጠቃሚ ነጥቦች የተነሱበት እየሰሩት ላለውም ሆነ ሊሰሩ ላሰቡት ስራ መሰረታዊ የሆነ ግንዛቤ የያዙበት በመሆኑ ደስተኛ መሆናቸውን ገልፀው ባንኩም ይህን ስልጠና ስላዘጋጀ ምስጋና ይገባዋል ብለዋል፡፡
ለወደፈቱም ባንኩ ተመሳሳይ ስልጠናዎችን በማዘጋጀት የሊዝ ፋይናንሲንግ ተበዳሪዎች አቅም የማጎልበት ስራ መስራት፣ ክትትልና ድጋፍ ማድረግ ቢቀጥል እንደባንክም ሆነ እንደ ሃገር ውጤታማ ስራ መስራት ያስችለዋል ሲሉ ሃሳባቸውን ገልፀዋል፡፡
ለአምስት ተከታታይ ቀናት በአምስት የስልጠና ማዕከላት ማለትም በአዲስ አበባ፣ በባህር ዳር፣ በጅማ፣ ደሴና ጅግጅጋ ሲሰጥ በቆየው ስልጠና ላይ 1500 የሚሆኑ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡
ክቡር ተገኝወርቅ ጌጡ (ፒ.ኤች.ዲ) የጃፓን ከፍተኛ የኒሻን ተሸላሚ ሆኑ!!
‹የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ የሆኑት ክቡር ተገኝወርቅ ጌጡ (ፒ.ኤች.ዲ) በጃፓን መንግስት የኒሻን ሽልማት የተሰጣቸው እ.ኤ.አ ህዳር 03 ቀን 2020 ሲሆን፤ ሽልማቱን አስመልክቶ እ.ኤ.አ መጋቢት 24 ቀን 2021 በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር መኖሪያ ቤት በተዘጋጀው ሥነ ሥርዓት ላይ ተበርክቶላቸዋል፡፡
የሀገርቷ ከፍተኛ የኒሻን ሽልማት የተበረከተላቸው በጃፓን እና በአፍሪካ እንዲሁም በጃፓን እና በኢትዮጵያ መካከል ኢኮኖሚያዊ ግንኙነቶችን በማጠናከር ረገድ ላበረከቱት አስተዋጽዖ እንደሆነ በሥነ ሥርዓቱ ላይ ተገልጿል፡፡
በእርሳቸው አመራር ሰጭነት በአፍሪካ ልማት ዙሪያ በቶክዮ ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ አማካይነት ከጃፓን መንግስት ጋር ያለውን ኢኮኖሚያዊ ግንኙነቶች ወደ ላቀ ደረጃ በማድረስ በርካታ ቢሊዮን ዶላሮች ለአፍሪካ ልማት እንዲውል ተደርጓል፡፡
በተለይም እንደ ጃፓን የውጭ ንግድ ድርጅት (ጄትሮ)፣ የጃፓን ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጄንሲ (ጃይካ)፣ UNDP እና ከኬይዛይ ዶዩዩይ (የጃፓን የኮርፖሬት አስፈጻሚዎች ማህበር) ጋር የሽርክና ማዕቀፎችን በመፍጠር የአፍሪካ ሀገራት ከጃፓን መንግስት ጋር ስትራቴጂያዊ ግንኙነት እንዲፈጥሩና በኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ክቡር ተገኝወርቅ ጌጡ (ፒ.ኤች.ዲ) ከፍተኛ አስተዋጽዖ አበርክተዋል፡፡
Page 12 of 26