ባንኩ የ2 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በኢትዮጵያ ባንኮች ማህበር አስተባባሪነት “አንድ ጫማ ለአንድ ተማሪ” በሚል መሪ ቃል ጥቅምት 16 ቀን 2012 ዓ.ም ለአዲስ አበባ ተማሪዎች በተዘጋጀው ፕሮግራም ላይ በመገኘት የ2 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርጓል፡፡
የገንዘብ ድጋፉን በሸራተን ሆቴል በተዘጋጀው ፕሮግራም ላይ በአካል በመገኘት ለአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ያስረከቡት የባንኩ ፕሬዚዳንት ዮሐንስ አያሌው (ፒ.ኤች.ዲ) ናቸው፡፡
ሰራተኛ ማህበሩ አዲስ የሥራ አስፈጻሚ አባላትን መረጠ
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ሰራተኛ ማህበር 40ኛውን መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ የኮቪድ-19 መመሪያን በጠበቀ ሁኔታ መስከረም 28 ቀን 2013 ዓ.ም ያካሄደ ሲሆን ጉባዔው 48 አባላት ያሉትን የምክር ቤት አባላትና ከምክር ቤቱም መካከል ሰባትሥራ አስፈጻሚዎችን መርጧል፡፡ ጠቅላላ ጉባዔው ለምክር ቤቱ ከየዲስትሪክቱና ዋናው መ/ቤት የሥራ ክፍሎች አንድ አንድ ተወካዮችን መምረጡም ታውቋል።
ጉባዔው የሰራተኛ ማህበሩን የስራ አስፈጻሚ እና የኦዲት ኮሚቴ ሪፖርቶችን አድምጧል፡፡
ጉባዔው የተጀመረው በባንኩ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ዮሐንስ አያሌው የመክፈቻ ንግግር ሲሆን እርሳቸውም የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በሃገሪቱ ብቸኛው የልማት ባንክ ከመሆኑ አንጻር በሃገሪቱ የሚታየውን የገበያ ክፍተት በመሙላት እና ልማቱን በማፋጠን ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ሲያበረክት በጉዞው ሂደት በርካታ ውጣ ውረዶችን ማሳለፉን አውስተዋል፡፡
አያይዘውም ባንኩ በየጊዜው የሚያጋጥሙትን ፈተናዎች ለማለፍና ህልውናውን ለማስቀጠል በየጊዜው የሚያጋጥሙ ችግሮቻችን ላይ በግልፅ በመነጋገርና መፍትሔ በማምጣት ከችግር በመውጣት ረገድ የባንኩ ሰራተኛ ማህበር በየኔነት ስሜት ብዙ መስራት እንደሚጠበቅበት አብራርተው፣ ባንኩም በጥናት ላይ የሚገኙ ማበረታቻዎች እንደ ሰራተኛው ብቃትና ችሎታ ተግባራዊ እንዲደረጉ የተቻለውን ጥረት እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡
በመቀጠል ንግግር ያደረጉት የባንክና መድን ሰራተኞች ማህበራት ኢንዱስትሪ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ደስታ በርሔ ሲሆኑ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ስብሰባዎችን ማድረግ አስቸጋሪ በሆነበት ወቅት አስፈላጊውን ጥንቃቄ ወስዶ ይህን ስብሰባ ማካሄዱ፣ በተጨማሪም በባንኩ እና በባንኩ ሰራተኛ ማህበር መካከል ለ12ኛ ጊዜ የህብረት ስምምነት እንዲከናወን በማድረጉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
በመቀጠልም እስካሁን በነበሩ ስራ አስፈፃሚ አካላት የተሰሩ ስራዎችን በማንሳትና በማመስገን ቀጣይ ወደ ስራ አስፈፃሚነት የሚመጡትም ከቀዳሚዎቹ ተሞክሮ በመውሰድ እና መልካም ልምዶች በማዳበር፣ ከዚህ ቀደም የነበሩ አሰራሮችን የበለጠ በማስተካከል ለተሻለ ስራ ዝግጁ እንዲሆኑ አሳስበዋል፡፡
ጉባዔው በአቶ ደስታ በርሔ አስመራጭነት የቀጣይ ስራ አስፈፃሚ አባላትን ምርጫ አካሂዷል፡፡ በምርጫውም፡- አቶ ይበልጣል ያየህ- ፕሬዚዳንት፣ አቶ አዲሱ ገብረ ሐና- ምክትል ፕሬዚዳንት፣ እንዲሁም አቶ ኃይሉ ተፈራ -ዋና ፀሐፊ ሆነው የተመረጡ ሲሆን የቀሩት ስራ አስፈፃሚ አባላት ደግሞ አቶ ግዛቸው ተክሉ፣ አቶ ኤርሚያስ አብድቄ፣ ወ/ሮ ኦሪት አበበ እና ወ/ሮ አዳነች ገረሱ ናቸው፡፡ በተጨማሪም ወ/ሮ ምህረት ኃ/የሱስ፣ አቶ መስፍን ሳህሌ እና አቶ ኢፋ ሽፈራው ደግሞ ለኦዲት ኮሚሽን ተመርጠዋል፡፡
በመጨረሻም የተመራጮች ቃለ መሃላ ሥነ ሥርዓት በማከናወን ስብሰባው ተጠናቋል፡፡
የባንኩ ሰራተኞች አጠቃላይ ስብሰባ በቪዲዮ ኮንፈረንስ ተካሄደ
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የስራ አመራር ቦርድ፣ የባንኩ የሥራ መሪዎችና ሠራተኞችን ያካተተው ስብሰባ በቪዲዮ ኮንፈረንስ መስከረም 25 ቀን 2013 ዓ.ም ተካሂዷል፡፡ የስብሰባው ዋነኛ ዓላማ አዲስ የተሾሙትን የባንኩን ፕሬዚዳንት ለባንኩ ሰራተኞች ማስተዋወቅ ሲሆን ከዚህ በተጨማሪም ባንኩ ስላለበት ወቅታዊ አቋም ለአዲሱ አመራር እና ሰራተኞች ገለጻ ተደርጓል፡፡
ስብሰባውን የመሩት የባንኩ የስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ዶ/ር ተገኘወርቅ ጌጡ ሲሆኑ፤ የባንኩን አዲስ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ዮሐንስ አያሌውን ለባንኩ ሰራተኞች በማስተዋወቅ ጀምረዋል፡፡
በመቀጠል ባንኩ ባለፈው በጀት ዓመት የአምስት ዓመቱን የሪፎርም ስትራቴጂክ እቅድ መሠረት በማድረግ ከፍተኛ ለውጥ ማምጣቱንና ይህንንም ከአዲሱ ፕሬዚዳንት ጋር በመሆን የበለጠ አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ አቅጣጫ ሰጥተዋል፡፡
በስብሰባው ላይ ከተሳታፊዎች በርካታ አስተያየትና ጥያቄዎች የተነሱ ሲሆን በዋናነትም ከባንኩ ፖሊሲና ፕሮሲጀር ማኑዋል አጠቃቀም፣ ከሰራተኛ ደሞዝ እና ጥቅማ ጥቅም ጭማሪ፣ እንዲሁም የባንኩ ገጽታ ለመቀየር መሰራት ስለሚገባቸው ስራዎችና ተያያዥ ጉዳዮች ናቸው፡፡
በማጠቃለያው ላይ የቦርድ ሰብሳቢው ዶ/ር ተገኘወርቅ ከተሳታፊዎች የተነሱትን በርካታ ጥያቄዎችና አስተያየቶች በመውሰድ ቦርዱና የባንኩ ማኔጅመንት ለቀጣይ ስራ እንደ ግብዓት እንደሚጠቀምባቸው ገልጸው የታዩ ጠንካራ ጎኖችን በማስቀጠል እና ድክመቶችን በማረም ባንኩን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ ሁሉም የባንኩ ሠራተኞች በኃላፊነት ስሜትና በቁርጠኝነት መስራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡
ዶ/ር ዮሐንስ አያሌው የባንኩ ፕሬዚዳንት ሆነው ተሾሙ
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የሥራ አመራር ቦርድ በራሳቸው ፈቃድ መልቀቂያ ባስገቡት አቶ ኃይለየሱስ በቀለ ምትክ ዶ/ር ዮሐንስ አያሌውን ከመስከረም 04 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት አድርጎ ሾመ፡፡
ዶ/ር ዮሐንስ አያሌው
ዶ/ር ዮሐንስ የኢትዮጵያ ልማት ፖሊሲ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር እና የቀድሞው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ የነበሩ ሲሆን እንዲሁ ከታህሳስ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የሥራ አመራር ቦርድ አባል በመሆን አገልግለዋል፡፡ ዶ/ር ዮሐንስ የባንኩ የቦርድ አባል በነበሩበት ጊዜ ባንኩ ተግባራዊ እያደረገ የሚገኘውን የአምስት ዓመት የሪፎርም ስትራቴጂክ እቅድ በመምራት እና እንዲሁም የተለያዩ ጥናቶች ላይ ከፍተኛ አስተዋጽዖ አበርክተዋል፡፡
Page 22 of 31