በባንኩና በባንኩ ሠራተኛ ማህበር መካከል የሕብረት ስምምነት ፊርማ ሥነ ሥርዓት ተካሄደ

 

በኢትዮጵያ ልማት ባንክ እና በባንኩ ሠራተኛ ማህበር መካከል ለ12ኛ ጊዜ የሕብረት ስምምነት ፊርማ ሥነ ሥርዓት ተካሄደ፡፡ የፊርማ ሥነ ሥርዓቱ የተካሄደው ሐምሌ 09 ቀን 2012 ዓ.ም በኢንተርኮንቲነንታል ሆቴል ነው፡፡

በሥነ ሥርዓቱ ላይ የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ኃይለየሱስ በቀለ፣ ምክትል ፕሬዚዳንቶች፣ የባንኩ ሠራተኛ ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ሙሉቀን አመነ እና ሥራ አስፈጻሚዎች፣ የባንክና መድን ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ደስታ በርሔ ተገኝተዋል፡፡

የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ኃይለየሱስ በዚህ ወቅት እንደተናገሩት ባንኩ ከሠራተኛ ማህበሩ ጋር በቅርበት ተሳስቦ እየሠራ እንደሚገኝ እና ይህ ተግባር ለወደፊቱም በተሻለ ሁኔታ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡ በተያያዘም በህብረት ስምምነቱ ላይ ለተሳተፉት አካላት በሙሉ ምሥጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

የማህበሩ ፕሬዚዳንት አቶ ሙሉቀን አመነ በበኩላቸው ማህበሩ የሠራተኛውን ጥቅማጥቅም ለማስከበር ከባንኩ ማኔጅመንት ጋር በውይይት እየሠራ የሚገኝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ደስታ በርሔ በበኩላቸው የባንኩ ማኔጅመንት እና ሠራተኛ ማህበሩ በመነጋገርና በመወያየት ከአቻ ባንኮች ጋር ተመሳሳይ ጥቅማጥቅሞች እንዲከበሩ ለሚያደርጉት ጥረት በሙሉ ፌዴሬሽኑ አድናቆቱን ገልጾ ፌዴሬሽኑ ለወደፊቱ እገዛውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አብራርተዋል፡፡

በህብረት ስምምነቱ ውስጥ አዲስ የገቡ እና የተሻሻሉ አንቀጾችና ንዑስ አንቀፆች ተካትተዋል፤ ከእነዚህ መካከል የሠራተኛ ቅጥር፣ ዝውውር፣ ደመወዝና ልዩ ማበረታቻ፣ የወሊድ ፈቃድ፣ የአባትነት ፈቃድ፣ ለሠራተኛ የሚሰጥ ብድር፣ ስለደረጃ ዕድገት፣ ትምህርትና ሥልጠና፣ የሕዝብ በዓላት፣ የትርፍ ሰዓት ሥራና ክፍያ፣ የቀን ውሎ አበል፣ የሐዘን ፈቃድ፣ ከሥራ ጋር ግንኙነት ስላለው በሽታና የአካል ጉዳት፣ በባንኩ የሚሸፈኑ የሕክምና ወጪዎች፣ የዲስፕሊን እርምጃ እንዲሁም ስለ ደንብ ልብስና የአደጋ መከላከያ ዘዴዎች ናቸው፡፡