ሕጻናት የቦንድ ግዥ መፈጸማቸውን ቀጥለዋል

በወ/ሮ አማካለች ከሊፋ አስተባባሪነት እና በወላጆቻቸው ድጋፍ ሕጻናት  በመጠናቀቅ ላይ ለሚገኘው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የቦንድ ግዥ በመፈጸም አስተዋጽዖ ማድረጋቸውን ቀጥለዋል፡፡

 

ሕጻናቱ የቦንድ ግዥውን የፈጸሙት ነሐሴ 27 ቀን 2012 ዓ.ም በባንኩ ዋናው መ/ቤት በአካል በመገኘት ነው፡፡

የባንኩ ተ/ም/ፕሬዚዳንት-ኮርፖሬት አገልግሎት አቶ ደሳለኝ ቦጋለ በዚህ ወቅት ግድቡ የሚሰራው ለነገ አገር ተረካቢ ለሆኑት የዛሬ ሕጻናት መሆኑን ገልጸው ድጋፉ በዚሁ ሁኔታ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ለወላጆች የአደራ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡

ከታላቁ ሕዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ጽ/ቤት አቶ መሰለ ብሩ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ሁነቱን በማስተባበር ሕጻናቱን ለማበረታታት ያደረገውን አስተዋጽዖ አመስግነው፣ ሕጻናት በወላጆቻቸው መልካም እገዛ በዚህ የሀገራችንን የወደፊት እጣ ፈንታ በሚወስነው ታላቅ ፕሮጀክት ላይ በመሳተፋቸውም ደስ ሊላቸው እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

የሕጻናቱ አስተባባሪ ወ/ሮ አማከለች “ግድቡ የእኔ ነው!” በሚል መሪ ቃል እየተካሄደ ባለው የቦንድ ግዥ ዘመቻ ላይ ልጆቻቸውንና ጎረቤቶቻቸውን በማስተባበር የተካሄደ ቢሆንም የቦንድ ግዥው ሊፈጸም የቻለው ግን በልጆቹ በራስ ተነሳሽነት መሆኑን አብራርተው፤ ድጋፉም ከዚህ በተሻለ ለወደፊቱ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል እምነታቸው እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ሕጻናቱ በአጠቃላይ የብር 40 ሺህ የቦንድ ግዥ መፈጸማቸው ታውቋል፡፡