የባንኩ ሰራተኞች አጠቃላይ ስብሰባ በቪዲዮ ኮንፈረንስ ተካሄደ

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የስራ አመራር ቦርድ፣ የባንኩ የሥራ መሪዎችና ሠራተኞችን ያካተተው ስብሰባ በቪዲዮ ኮንፈረንስ መስከረም 25 ቀን 2013 ዓ.ም ተካሂዷል፡፡ የስብሰባው ዋነኛ ዓላማ አዲስ የተሾሙትን የባንኩን ፕሬዚዳንት ለባንኩ ሰራተኞች ማስተዋወቅ ሲሆን ከዚህ በተጨማሪም ባንኩ ስላለበት ወቅታዊ አቋም ለአዲሱ አመራር እና ሰራተኞች ገለጻ ተደርጓል፡፡

ስብሰባውን የመሩት የባንኩ የስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ዶ/ር ተገኘወርቅ ጌጡ ሲሆኑ፤ የባንኩን አዲስ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ዮሐንስ አያሌውን ለባንኩ ሰራተኞች በማስተዋወቅ ጀምረዋል፡፡

በመቀጠል ባንኩ ባለፈው በጀት ዓመት የአምስት ዓመቱን የሪፎርም ስትራቴጂክ እቅድ መሠረት በማድረግ ከፍተኛ ለውጥ ማምጣቱንና ይህንንም ከአዲሱ ፕሬዚዳንት ጋር በመሆን የበለጠ አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ አቅጣጫ ሰጥተዋል፡፡

በስብሰባው ላይ ከተሳታፊዎች በርካታ አስተያየትና ጥያቄዎች የተነሱ ሲሆን በዋናነትም ከባንኩ ፖሊሲና ፕሮሲጀር ማኑዋል አጠቃቀም፣ ከሰራተኛ ደሞዝ እና ጥቅማ ጥቅም ጭማሪ፣ እንዲሁም የባንኩ ገጽታ ለመቀየር መሰራት ስለሚገባቸው ስራዎችና ተያያዥ ጉዳዮች ናቸው፡፡

በማጠቃለያው ላይ የቦርድ ሰብሳቢው ዶ/ር ተገኘወርቅ ከተሳታፊዎች የተነሱትን በርካታ ጥያቄዎችና አስተያየቶች በመውሰድ ቦርዱና የባንኩ ማኔጅመንት ለቀጣይ ስራ እንደ ግብዓት እንደሚጠቀምባቸው ገልጸው የታዩ ጠንካራ ጎኖችን በማስቀጠል እና ድክመቶችን በማረም ባንኩን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ ሁሉም የባንኩ ሠራተኞች በኃላፊነት ስሜትና በቁርጠኝነት መስራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡