በባንኩ የፀረ ሙስና ቀን ተከበረ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ17ኛ በሀገር አቀፍ ደረጃ ደግሞ ለ16ተኛ ጊዜ የትውልድ የስነ ምግባር ግንባታን በጠንካራ ዲሲፕሊን በመምራት ሌብነትንና ብልሹ አሰራርን በመታገል የብልፅግና ጉዟችንን እናፋጥናለን!” በሚል መሪ ቃል ዓለም አቀፉን የፀረ ሙስና ቀን በኢትዮጵያ ልማት ባንክ ተከብሯል፡፡

 

በባንኩ የስነ ምግባርና ቅሬታ መከታተያ ቢሮ አስተባባሪነት ህዳር 25 ቀን 2013 ዓ.ም በተዘጋጀው በዚህ ስነ ስርዓት ላይ የባንኩ ም/ፕሬዚዳንት ኮርፖሬት አገልግሎት  አቶ ሰፊዓለም ሊበን ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉ ሲሆን በንግግራቸውም የባንኩ ሰራተኞች ሙስናን በመከላከል ረገድ በታማኝነት ኃላፊነታቸውን መወጣት እንደሚኖርባቸው አሳስበዋል፡፡

በተለይም ከዚህ ቀደም የተከሰቱ ግድፈቶችን በመፈተሸና በማጥናት ለውስጣዊና ውጫዊ ጫናዎች መከሰት በር የሚከፍቱ አሰራሮችን ለመዝጋት እንዲቻል ግልፅ የሆነ አሰራሮችንና መመሪያዎችን በማዘጋጀት የባንኩን መልካም ስምና ዝናውን ለማደስ የሚያስችሉ ስራዎችን ለመስራት ከሁሉም ሰራተኛ ቁርጠኝነት እንደሚጠበቅ አውስተው ቀኑን ስናከብር ከራሳችን ህይወት በመጀመር ሁላችንም የተጣለብንን ኃላፊነት በታማኝነት መወጣት መቻል ራሳችንንም ሆነ ባንካችንን ከአደጋ መጠበቅ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በስነ ስርዓቱ ላይ በዳኛቸው አሰፋ /ፒ.ኤች.ዲ/ ሙስና ከፖለቲካ ከህግና ከሞራል አንጻር ያለው አንድምታን በሚመለከት እንዲሁም በአቶ ወርቁ ፈቃደ የሥነ ምግባርና ቅሬታ መከታተያ ቢሮ ኃላፊ ለውይይት መነሻ የሚሆኑ ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው በተሳታፊዎች ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡