የባንኩ የማሻሻያ ስራዎች ቀጣይነታቸው እንዲረጋገጥ በትኩረት መስራት እንደሚያስፈልግ ገንዘብ ሚኒስቴር ገለጸ

  • የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ባለፉት ስድስት ወራት ያከናወናቸው ዋና ዋና የማሻሻያ ስራዎች የባንኩን ትርፋማነት ለማሳደግ እንዳስቻለ ተገልጿል፡፡

 

በገንዘብ ሚኒስትሩ በክቡር አቶ አህመድ ሽዴ በተመራ ግምገማ ላይ እንደተገለጸው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ትርፋማነቱ ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በብር 304.16 ሚሊዮን ብልጫ ማለትም በ150 በመቶ ከፍ ያለ ሆኖ ተገኝቷል፡፡

አቶ አህመድ ሽዴ የባንኩ ትርፋማነት የተገኘው ተለያዩ የለውጥ ስራዎች በመተግበራቸው እንደሆነ በግምገማው ወቅት አብራርተዋል:: በተለይም ባንኩ የነበረውን ብድር የማስተዳደርና የመቆጣጠር አቅም ማሳደጉ ለዚህ ውጤት እንዳበቃው ተናግረዋል፡፡

 

በተጨማሪም የኢትዮጵያ የልማት ባንክ በስድስት ወር ውስጥ የህዳሴ ግድብ ቁጠባን በተመለከተ ብር 500 ሚሊየን ለመፈፀም አቅዶ ብር 883.47 ሚሊየን ለመሰበብሰብ መቻሉ የሚበረታታ መሆኑም በግምገማው ተመልክቷል፡፡ በተለይም ኢትዮጵያዊያን በራሳቸው አቅም እየገነቡት ያለው የህዳሴ ግድብ ወቅቱን ጠብቆ ማጠናቀቅ እንዲቻል ባንኩ ጥረቱን አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባው ክቡር አቶ አህመድ ሽዴ አሳስበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ልማት ባንክን የማሻሻያ ስራዎች ውጤታማነታቸውን ቀጣይ ለማድረግ ባንኩ በአዳዲስ እና በቴክኖሎጂ የታገዙ የአሰራር ስርዓቶችን ማጎልበት፣ የባንኩን የውጭ ምንዛሪ አቅም ማሳደግ እና የባንኩን አማራጭ የሀብት ምንጭ ለማጎልበት የሚያስችሉ ተግባራት ቀዳሚ ትኩረት የሚሹ መሆናቸውን አቶ አህመድ ሽዴ አስረድተው፤ ባንኩን በዘላቂነት ከሀብት ጥገኝነት ለማውጣት የማሻሻያ ስራዎች በወጣላቸው መርሀ ግብር መሰረት መተግበር እንደሚኖርባቸውም ማሳሰባቸው  ታውቋል፡፡