ባንኩ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሄደ

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የአነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንተርፕራይዞችን ፋይናንስ ለማድረግ ያለመ ውይይት ከመንግስትና የግሉ ዘርፍ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር መጋቢት 01 ቀን 2013 ዓ.ም በቢሾፍቱ ከተማ አካሂዷል፡፡

በውይይቱ ላይ የባንኩ ፕሬዚዳንት፣ ምክትል ፕሬዚዳንቶችና ዲስትሪክት ስራ አስኪያጆች እንዲሁም የፌዴራል እና ክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የአምራች ዘርፍ፣ የግል ባንኮች እና አነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት የሥራ መሪዎች ተገኝተዋል፡፡

ስብሰባውን በንግግር የከፈቱት የፌዴራል አነስተኛ መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ልማት ማስፋፊያ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ አስፋው አበበ እንዳሉት ለሀገር በቀል ኢኮኖሚ ትልቅ ተስፋ የተጣለበትን አነስተኛ መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ልማት ፋይናንሲንግ ዙሪያ ለመነጋገር በተዘጋጀው በዚህ መድረክ ላይ ፋይናንስ ለኢንዱስትሪው ዘርፍ ልማት የደም ስር መሆኑንና ያለ ፋይናንስ የኢንዱስትሪውን ልማት ከፍ ማድረግ እንደማይቻል ጠቅሰዋል፡፡

የውይይት መድረኩ መዘጋጀት ዋነኛ ዓላማ አነስተኛና መካከለኛ አምራች ዘርፎችን ፋይናንስ በማድረግ ሂደት ያጋጠሙ ችግሮችን ከአሠራርና ከአፈጻጸም አኳያ በመገምገም ችግሮቻቸውን ማስተካከል በሚቻልበት ዙሪያ እና ተቋርጦ የነበረውን የማሽነሪ ሊዝ ፋይናንሲንግ ውጤታማ በሆነ መንገድ ፋይናንስ ለማድረግ በዓለም ባንክ ለዘርፉ የተደረገውን የ8.6 ቢሊዮን ብር ድጋፍ በአግባቡ ለመጠቀም የባለድርሻ አካላት ቅንጅት ለማምጣት መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ አብራርተዋል፡፡

በአምራች ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ላይ ተሰማርተው የፋይናንስ፣ የቴክኖሎጂ፣ የመስሪያ ቦታ እና የገበያ ትስስር ክፍተት ያለባቸውን ኢንተርፕራይዞች ችግር ለማቃለል የተገኘውን ሀብት በአግባቡ ለመጠቀም ተቀናጅቶ መስራት ወሳኝ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዝዳንት ዮሐንስ አያሌው /ፒ.ኤች.ዲ/ በበኩላቸው በተለያዩ ምክንያቶች ተቋርጦ የቆየውን የካፒታል ዕቃ ኪራይ አገልግሎት በአዲስ መልክ ለመጀመር ቀደም ሲል ዘርፋን ሲያጋጥሙ የነበሩ ችግሮችን በመቅረፍ ብድር ወደመስጠት ለመሄድ ደንበኞች መብትና ግዴታቸውን እንዲያውቁና ስለሚሰሩት ሥራ በቂ ግንዛቤና ራዕይ ሊኖራቸው ስለሚገባ ባንኩ በሰባት ማዕከላት ስልጠና ለመስጠት ቅድመ ዝግጅት ማጠናቀቁን ገልጸዋል፡፡

ባንኩ ከስልጠና በኋላ ለሚሰጠው የማሽነሪ ሊዝ ፋይናንስ፣ የሥራ ማስኬጃ ብድር (Working capital) እና የፕሮጀክት ብድር ባለድርሻ አካላት ከባንኩ ጎን በመሆን አስፈላጊውን ትብብር ማድረግ እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡ በተለይም ቀደም ሲል ሲስተዋል የነበረውን የቅንጅት ችግር በመቅረፍ በተናበበና በትብብር መንፈስ አምራች ዘርፉን መደገፍ እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡

በመድረኩ ላይ የተገኙት ባለድርሻ አካላት በሰጡት አስተያየት በአጭር ጊዜ ውስጥ ባንኩ ተግባራዊ እያደረገ ያለውን የሪፎርም ሥራ በማድነቅ ባንኩ የሚሰራቸውን ሥራዎች በግንባር ቀደምትነት ለመደገፍ ያላቸውን ቁርጠኝነት ገልጸዋል፡፡   

የአነስተኛ መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ልማት ለማስፋፋት የዛሬ አራት ዓመት መንግስት በሰጠው አቅጣጫ ከጥቃቅንና አነስተኛ ወደ አነስተኛና መካከለኛ የተሸጋገሩ (the missing middle) ኢንተርፕራይዞች የፋይናንስ ችግር ለመፍታት በርካታ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ሰፊ ውይይት ተደርጎ የተጀመረ ሥርዓት መሆኑ ይታወሳል፡፡