ሀገር አቀፍ ስልጠናው በይፋ ተጀመረ

በኢትዮጵያ ልማት ባንክ ለአነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንተርፕራይዞች ከመጋቢት 13 እስከ 17 ቀን የሚካሄደው ስልጠና ሰኞ መጋቢት 13 ቀን 2013 ዓ.ም በይፋ ተጀምሯል፡፡

ስልጠናው ሀገር አቀፍ ሲሆን በአምስት ማእከላት ማለትም በአዲስ አበባ፣ ባህር ዳር፣ ጂማ፣ ደሴና ጂግጂጋ እየተካሄደ ይገኛል፡፡

የስልጠናውን መከፈት አስመልክቶ የባንኩ ፕሬዚዳንት ዮሐንስ አያሌው (ፒ.ኤች.ዲ) ፍሬንድሺፕ ሆቴል ለአዲስ አበባ ሰልጣኞች በአካል በመገኘት እና በዙም /zoom meeting/ ደግሞ ለክልሎች መልእክት አስተላልፈዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ በመክፈቻው እለት ባስተላለፉት መልእክት በአሁኑ ሰዓት በአገሪቷ ላይ ያሉ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ዘርፈ ብዙ ችግሮችና ተግዳሮቶች እንዳሉባቸው እንደሚታወቁና ዋናዎቹ የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎችና የባለድርሻ አካላት የግንዛቤ ደረጃ አናሳ መሆን፣ ስለሊዝ ፋይናንስ የእውቀት ክፍተት መኖር፣ አንዳንድ የሊዝ ተጠቃሚዎች እንዲገዛላቸው የሚፈልጉትን የማሽነሪ ዓይነትና ጥራት ለይቶ አለማወቅ፣ አገልግሎት ፈላጊዎች የሚጠበቅባቸውን የቅድመ መዋጮ በወቅቱ አለማዋጣትና የፕሮጀክት ሃሳብ መቀያየር፣ ረጅም የሆነ የማሽነሪ የግዢ ሂደት መኖር፣ የኃይል አቅርቦት አለመኖርና የኃይል መቆራረጥ፣ የመስሪያ ቦታ ችግር፣ የባለድርሻ አካላት የተቀናጀ አገልግሎት አለመስጠት፣ የሥራ ማስኬጃ ብደር ለማግኘት የመያዣ ዋስትና ችግር እና የመሳሰሉት እንደሆኑ ገልጸው፤ ባንኩም የተለያዩ መፍትሔ እርምጃዎች በመውሰድ ላይ እንደሚገኝና ይህ ስልጠናም ግንዛቤ ከመፍጠር አኳያ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው  ተናግረዋል፡፡

ስልጠናው የአነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንተርፕራይዞች  ከባንኩ ጋር የሥራ ግንኙነት ከመጀመራቸው በፊት በቢዝነስ ፕላን አዘገጃጀትና ርዕይ ቀረጻ፣ በፋይናስና የሂሳብ አስተዳደር፣ ንግድ ሥራ አመራር፣ በገበያ ፍለጋ፣ በሰው ሀብት አስተዳደር፣ እንዲሁም በአጠቃላይ በሀገሪቱ የቢዝነስና የፖሊሲ ከባቢያዊ ሁኔታ እና ማበረታቻዎች ላይ አቅማቸውን በመገንባት እውቀትና ክህሎት እንዲኖራቸው ስልጠናው መዘጋጀቱን የባንኩ ፕሬዚዳንት ዮሐንስ አያሌው (ፒ.ኤች.ዲ) ጨምረው አብራርተዋል፡፡

በመቀጠል የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር የተከበሩ አቶ ሽመልስ አብዲሳ፣ የሱማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ምክትል ርዕሰ መስተዳድር የተከበሩ አቶ ሙስጠፌ መሐመድ እና በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳድር የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ የተከበሩ አቶ ጃንጥራር አባይ በዙም የመክፈቻ ንግግር አድርገዋል፡፡

ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች በንግግራቸው ባስተላለፉት መልእክት ባንኩ ይህንን ለአነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንተርፕራይዞች በእውቀት የታገዘ ስልጠና በማዘጋጀቱ አመስግነው ሌሎች መሰል የፋይናንስ ተቋማትም ይህንኑ በጎ ተሞክሮ እንዲወስዱ አሳስበዋል፡፡ በየክልላቸው ለሚገኙ የስልጠና ተሳታፊዎችም ከባንኩ ጎን በመቆም አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ስልጠናው በሀገር አቀፍ ደረጃ እንዲሁ ከመጋቢት 20 እስከ 24 ቀን 2013 ዓ.ም በአዳማ፣ ቡታጂራ እና ወላይታ ሶዶ ከተሞች የሚካሄድ ሲሆን በሁለቱ ዙር ስልጠና በአጠቃላይ ከ3500 በላይ ሰልጣኞች እንደሚሳተፉ ይጠበቃል፡፡