የባንኩ ሠራተኞች ደም ለገሱ

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ሠራተኞች ደማችንን ለጀግኖቻችን በመለገስ አጋርነታችንን እናረጋግጣለን!” በሚል መሪ ቃል የሀገር ህልውናን ለማስከበር በተለያዩ ግንባሮች እየተፋለሙ ለሚገኙ የመከላከያ ሠራዊትና በዘመቻው ላይ ለተሳተፉ ጀግኖች አለኝታነታቸውን ለማረጋገጥ ኅዳር 9 ቀን 2014 ዓ.ም በባንኩ ዋና መሥሪያ ቤት ደም ለግሰዋል፡፡

የደም ልገሳ ሥነ ሥርዓቱን በንግግር ያስጀመሩት የባንኩ ፕሬዚዳንት ክቡር ዮሐንስ አያሌው (ፒ.ኤች.ዲ) ሲሆኑ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ሠራተኞች የሀገር ህልውናን የማስከበር ዘመቻ ከተጀመረ ጊዜ ጀምሮ የወር ደመወዛቸውን ከማዋጣት አንስቶ የተለያዩ ድጋፎች በማድረግ ላይ መሆናቸውን ተናግረው፤ በደም ልገሳ የቀጠለው ድጋፍ ወደፊትም ባንኩም ሆነ ሠራተኞቹ የሚጠበቅባቸውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡ በማከልም ባንኩና ሠራተኞች ይህንን ሀገራዊ ጥሪ ለመመለስ ላሳዩት ተነሳሽነትና ፈቃደኝነት ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

በደም ልገሳ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ከ130 በላይ የባንኩ ሰራተኞች ደም ለመለገስ በፍቃደኝነት የተመዘገቡ ሲሆን ከ54 ዩኒት በላይ ደም መሰብሰቡን ለማወቅ ተችሏል፡፡

የህልውና ዘመቻው ከተጀመረ ጊዜ ጀምሮ ባንኩ ለሀገር መከላከያ ሠራዊት የብር 106 ሚሊዮን ድጋፍ ማድረጉንና 12 የባንኩ ሠራተኞች ደግሞ ግንባር ድረስ መዝመታቸው ታውቋል፡፡

የደም ልገሳ መርኃ ግብሩ ላይ በመገኘት ደም የለገሱ የባንኩ ሠራተኞች በበኩላቸው ለሀገር ህልውና በተለያዩ ግንባሮች እየተዋደቀ ለሚገኘው ጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ደም በመለገሳቸው ደስተኞች መሆናቸውን በመጠቆም ለወደፊቱም አጋርነታቸው ለማሳየት ቁርጠኛ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡