በባንኩና ኢቢሲ መካከል የመግባቢያ ስምምነት ተፈረመ

በኢትዮጵያ ልማት ባንክ እና በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) መካከል በሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፍ አብሮ ለመሥራት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ታህሳስ 04 ቀን 2014 ዓ.ም በራዲሰን ብሉ ሆቴል ተፈርሟል፡፡

 

የባንኩ ፕሬዚዳንት ክቡር ዮሐንስ አያሌው (ፒ.ኤች.ዲ) እና የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ክቡር አቶ ፍስሃ ይታገሱ የመግባቢያ ስምምነቱን  ፈርመዋል፡፡

በመግባቢያ ስምምነቱ መሠረት ኢቢሲ ባንኩ ለሚሰራቸው ሚዲያ ነክ ሥራዎች፣ ልዩ ልዩ መግለጫዎች እና ማስታወቂያዎች በጣቢያው /የራዲዮና የቴሌቪዥን ሚዲየሞች/ ቅድሚያ በመስጠት የዜና ሽፋን የሚሰጥ ሲሆን ባንኩም የተለያዩ ሁነቶች ሲኖሩት ለኢቢሲ ቅድሚያ በመስጠት ሽፋን እንዲያገኝ ያደርጋል፡፡

የሁለቱም ተቋማት መሪዎች ስለ ተቋሞቻቸው አጠር ያለ ጽሑፎችን አቅርበዋል፡፡

የባንኩ ፕሬዚዳንት ዮሐንስ አያሌው (ፒ.ኤች.ዲ) ባቀረቡት ጽሑፍ ልማት ባንክ የ5 ዓመት ስትራቴጂክ ነድፎ ወደ ሥራ ከገባበት በተለይም ከአንድ ዓመት ወዲህ ውጤታማ ባንክ ሆኗል፡፡ በታሪኩ ከፍተኛ የተባለ ትርፍም አስመዝግቧል፡፡ በተያዘው በጀት ዓመትም ካለፈው ዓመት የተሻለ ውጤት ለማምጣት ተግቶ እየሰራ ይገኛል፤ ምንም እንኳ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል እየተካሄደ ካለው የሠላም ማስከበር እና የህልውና ዘመቻ ጋር በተያያዘ ተግዳሮቶች ቢኖሩብንም ብለዋል፡፡

የኢቢሲ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ፍስሃ ይታገሱ በበኩላቸው የሚዲያ ተቋሙ በሀገር ግንባታ፣ በሀገራዊ መግባባት እና ዴሞክራታይዜሽን ሂደት ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራቱን ገልጸው፤ ሁለቱም አንጋፋ ተቋማት በሀገር ግንባታ ሂደት ላይ የበኩላቸውን ሚና እየተጫወቱ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ከተመሠረተ ከ113 ዓመት በላይ፣ እንዲሁ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ደግሞ ከ87 ዓመት በላይ እድሜ ያስቆጠሩ አንጋፋ ተቋማት መሆናቸው ይታወቃል፡፡