በባንኩ የገንዘብ ድጋፍ የተሰራው “ኂሩት አባቷ ማነው?” ፊልም ተመረቀ

በኢትዮጵያ ልማት ባንክ የገንዘብ ድጋፍ የተሰራው በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነው ባለጥቁርና ነጭ ቀለም “ኂሩት አባቷ ማነ?” ፊልም ዲጂታላይዝ በመደረጉ ሐሙስ ጥር 5 ቀን 2014 .ም በሸራተን አዲስ ሆቴል በይፋ ተመርቋል፡፡

በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳር ከንቲባ ክብርት ወ/ሮ አዳነች አበቤን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት ሥራ ኃላፊዎች፣ የባንኩ ከፍተኛ አመራሮች፣ ታዋቂ አርቲስቶች እና በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ተገኝተዋል፡፡

በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላየአዲስ አበባ ከተማ አስተዳር ከንቲባ ክብርት ወ/ሮ አዳነች አበቤ ፕሮግራሙን አስመልክቶ መልእክት በማስተላለፍ ፊልሙን መርቀው የከፈቱ ሲሆን በንግግራቸውም በኢትዮጵያ የመጀመሪያው በሆነው ታሪካዊ ፊልም ላይ በመገኘታቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልፀው፣ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ለዚህ ታሪካዊ ፊልም ከመነሻው ጀምሮ እስካሁን ድረስ ላበረከተው አስተዋጽዖ አመስግነው፣ ፊልሙ በተለይ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ወደ ሀገራቸው በመጡበት ሰዓት መመረቁ ሀገራችን ከጥንት ጀምሮ በኪነጥበቡ ዘርፍ አሻራዋን ስታሳርፍ ማለፏን ከመገንዘብ ባለፈ ስለ ቀደምት የኪነ ጥበብ ስራዎች መረጃ ለማግኘትና ለቀጣይ በኪነ ጥበቡ ዘርፍ ለሚደረጉ ጥናታዊ ጽሑፎች መነሻ ግብዓትም ይሆናቸዋል ብለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህል፣ ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ክብርት ዶ/ር ሂሩት ካሳው በበኩላቸው በ1957 .ም በኢትዮጵያ ልማት ባንክ የገንዘብ ድጋፍ የተሰራው ይህ ታሪካዊ ፊልም በወቅቱ ፊልሙ ከባንኩ በተገኘ ብድር የሰራው የሲኒማ ቤቶች አስተዳደር እዳው ተሰርዞለት ፊልሙ በስጦታ እስከተበረከተበት እለት ለ40 ዓመታት ሳይበላሽ በጥንቃቄ በማስቀመጡ ባንኩን እጅግ ያስመሰግነዋል ብለዋል፡፡

አያይዘውም በ2012 .ም ዲጂታይዝድ ተደርጎ በአሁን ሰዓት በድጋሚ ለእይታ እንዲበቃ ባንኩ ላደረገው ከፍተኛ ድጋፍ በኪነጥበብ ባለሙያዎችና በዘርፉ ሥም አመስግነው ወደፊትም ባንኩ ለዘርፉ የሚያደርገውን ድጋፍ እንደሚቀጥል ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡

ባንኩ በኢትዮጵያ የፊልም ታሪክ ግንባር ቀደም ሆኖ ፋይናንስ በማድረግ ላበረከተው አስተዋጽዖ የምሥጋና ምሥክር ወረቀት ተበርክቶለታል፡፡