ባንኩ ከዲያስፖራ ማኅበረሰብ ጋር ውይይት አካሄደ

ባንኩ የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ጥሪን ተከትለው ወደ ሀገራቸው ከገቡ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን /ዲያስፖራ ማኅበረሰብ/ ጋር ጥር 27 ቀን 2014 ዓ.ም በባንኩ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ውይይት አካሂዷል፡፡

በውይይቱ ላይ የባንኩ ፕሬዚዳንት፣ ምክትል ፕሬዚዳንቶች፣ የዲያስፖራ ማኅበረሰብ ማህበር ተወካዮች፣ የማህበሩ አባል የሆኑ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን /የዲያስፖራ ማኅበረሰብ/ ተገኝተዋል፡፡

በውይይቱ ወቅት የባንኩ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ዮሐንስ አያሌው /ፒ.ኤች.ዲ/ ስለባንኩ የቀድሞ አሠራር፣ አሁንናዊ ሁኔታ እና ለወደፊቱ ሊሰሩ ስለታቀዱ ሥራዎች፣ እንዲሁም የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድን መሠረት በማድረግ ስለተጀመሩ የለውጥ ሂደቶች አጠር ያለ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን ከዚህ በተጨማሪ በጋምቤላ ክልል የሚገኙ ፕሮጀክቶችን ተረክቦ ማስቀጠል ለሚችል ዳያስፖራ አስፈላጊውን ሂደት ተከትሎ መሥራት የሚችልበት ሁኔታ የተመቻቸ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

በመቀጠል ለዲያስፖራው ማህበረሰብ ከባንኩ ስለሚፈልጉት እገዛ እና ተያያዥ ጉዳዮች ያሏቸውን ጥያቄዎች እንዲያነሱ መድረኩን ክፍት አድርገዋል፡፡

በውይይቱ ላይ የተገኙት ተሳታፊዎች በርካታ ጥያቄዎች እና አስተያየቶችን  ያነሱ ሲሆን በዋናነትም የባንኩ የብድር አሰጣጥ ሂደትን ቀልጣፋ አለመሆን፣ የውጭ ምንዛሪ አሰጣጥ፣ የወለድ ምጣኔ እና የብድር አመላለስ፣ እንዲሁም  የእፎይታ ጊዜን በተመለከተ ግልጽ የሆነ ማብራሪያ እንዲሰጣቸው የጠየቁ ሲሆን ከተሳታፊዎች ለቀረቡ ጥያቄዎች ከባንኩ ፕሬዝዳንት በተሰጠው ምላሽ የባንኩ ወለድ ምጣኔ 11.5 መሆኑን ገልጸው ይህም በሃገራችን ካሉ የንግድ ባንኮች አንፃር ሲታይ አነስተኛ መሆኑ ለዳያስፖራው ጠቀሜታ እንዳለው ገልፀዋል፡፡ የእፎይታ ጊዜን በተመለከተም እንደፕሮጀክቱ ዓይነት የሚታይ ሆኖ ከ6 ወር እስከ 3 ዓመት እንደሚሆን ምላሽ ተሰጥቶበታል፡፡

ተሳታፊዎቹ ባንኩ ይህን መድረክ በማዘጋጀቱ ምስጋናቸውን ያቀረቡ ሲሆን ባንኩን ባላቸው የእውቀት እና ቴክኖሎጂ ሙያ ዘርፎች የበኩላቸውን እገዛ ለማድረግ ፈቃደኛ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡