የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ሰራተኞች የሴቶች ቀን /March 8/ አከበሩ

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ሰራተኞች በሀገር አቀፍ ደረጃ ለ46ተኛ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ111ኛ ጊዜ የሚከበረውን ዓለም አቀፉን የሴቶች ቀን /March 8/ መጋቢት 29 ቀን 2014ዓ.ም በባንኩ የመሰብሰቢያ አዳራሽ አክብረዋል፡፡

“እኔ የእህቴ ጠባቂ ነኝ” እና “የስርዓተ ፆታ እኩልነት ለዘላቂ ልማት” በሚሉ መሪቃሎች በተከበረው በዓል ላይ የባንኩ ከፍተኛ አመራሮች፣ የኢትዮጵያ ሰራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽ የሴቶች ጉዳይ መምሪያ ሃላፊ ወ/ሮ ራሄል አየለ፣ የኢትዮጵያ ፋይናንስ ተቋማት ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ደስታ በርሄ እንዲሁም የባንኩ ሴት አመራሮችና ሰራተኞች ተገኝተዋል፡፡

በፕሮግራሙ ላይ የባንኩን ፕሬዝዳንት በመወከል የተገኙት የኮርፖሬት አገልግሎት ም/ፕ አቶ ሰፊዓለም ሊበን የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት ያስተላለፉ ሲሆን፤ በመልእክታቸውም በማህበረሰባችን ውስጥ ተደራራቢ ሃላፊነትን በመወጣት ከፍተኛ አስተዋፅኦ በማድረግ ትልቁን ቁጥር የሚይዙት ሴቶች መሆናቸውን ገልፀው እንደ ተቋምም እንደ ማህበረሰብም ሴቶችን ማገዝና መደገፍ ውጤታማ ስራ ለመስራት መሰረት እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡ አክለውም ሴቶችን ለማብቃት እና የባንኩን የሴት አመራሮች ቁጥር ለመጨመር እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡  

የኢትዮጵያ ሰራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽ የሴቶች ጉዳይ መምሪያ ሃላፊ ወ/ሮ ራሄል አየለ በበኩላቸው ባስተላለፉት መልእክት ሴቶች እድሉ ከተሰጣቸውና ራሳቸውን እንዲያበቁ እገዛ ቢደረግላቸው ከፍተኛ ለውጥ ማምጣት የሚያስችል እምቅ ሃይልና ችሎታ ባለቤት ናቸው ያሉ ሲሆን፤ ባንኩ ሴቶችን ወደ አመራር ቦታ ለማምጣት ትኩረት ሰጥቶ አንዲሰራ ጠይቀዋል፡፡ አያይዘውም “እኔ የእህቴ ጠባቂ ነኝ” በሚለው መርህ መሰረት ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በተለይም ወንድ ሰራተኞች የሴቶችን ጥቃል ለመከላከል ዘብ እንዲቆሙ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በፕሮግራሙ ማጠቃለያ ላይ ሀገራችን በገጠማት የህልውና ማስከበር ጦርነት ወቅት ሃገራቸውን እና ወገናቸውን ከጥቃት ለመታደግ የህይወት መሰዋዕትነት ለመክፈል በመቁረጥ በፍቃደኝነት ለዘመቱ የባንኩ ሰራተኞች የእውቅና አሰጣጥ ስነስርዓት ተካሂዷል፡፡