ባንኩ በሊዝ ፋይናንሲንግ አገልግሎት የገዛቸውን ተሸከርካሪዎች አስረከበ

  

 

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በሊዝ ፋይናንሲንግ አገልግሎት በማስጎብኘት የሥራ መስክ ለተሰማሩ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች  የገዛቸውን ተሸከርካሪዎች ጥር 30 ቀን 2011 ዓ.ም. አስረከበ፡፡

በርክክብ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የባንኩ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ ፋይናንሲንግ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ተሾመ አለማየሁ ባስተላለፉት መልዕክት የቱር ኢንዱስትሪ ምንም እንኳን የአገልግሎት ዘርፍ (Service) ቢሆንም በልዩ ሁኔታ የባንኩ አንዱ የትኩረት ዘርፍ ሆኖ አገልግሎቱ በመሰጠት ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡

አቶ ተሾመ አያይዘው ባንኩ ከዚህ ቀደም ለአስጎብኚ ድርጅቶች ላጸደቀው ሊዝ በተበጣጠሰ መልኩ ተሸከርካሪዎችን በአገር ውስጥ አቅራቢዎች በቀረበው መጠንና ጊዜ ለደንበኞቹ ሲያቀርብ እንደነበርና አሁን ግን የውጭ ምንዛሪ በማመቻቸት ከብር 42 ሚሊዮን 202 ሺህ በላይ በማውጣት ለ16 የሊዝ ደንበኞች 36 ለማስጎብኘት ሥራ የሚውሉ ተሸከርካሪዎችን የገዛ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ 26 ተሸከርካሪዎችን ለ12 ደንበኞች በዚህ ዙር ርክክብ የፈጸመ ሲሆን ቀሪዎቹን 10 ተሸከርካሪዎች ደግሞ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ እንደሚያስተላልፍ አክለው ገልጸዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ተወካይ፣ ወ/ሮ ማሚት ይልማ በበኩላቸው ባንኩ ለቱሪዝም ዘርፍ መጎልበት እያበረከተ ያለውን አስተዋጽኦ አድንቀው ተሽከርካሪዎቹ ለተቋቋሙበት ዓላማ እንዲውሉ አሳስበዋል፡፡

ተሽከርካሪዎቹ ተገዝተው ወደ አገር ውስጥ የገቡት በኢትዮጵያ ሞተርና ኤንጅነሪንግ ኩባንያ /ሞኤንኮ/ በኩል እንደሆነ ይታወቃል፡፡