የባንኩ ዓመታዊ የሥራ አፈጻጸም ምክክር መድረክ ተካሄደ
በባንኩ የ2013 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት እና የቀጣይ ዓመት የትኩረት አቅጣጫ እንዲሁም በባንኩ የለውጥ ሥራዎች ትግበራ የባለድርሻ አካላት ድጋፍ ዙሪያ በአዳማ ከተማ የምክክር መድረክ ተካሂዷል፡፡
የምክክር መድረኩ የተካሄደው ሐምሌ 03 ቀን 2013 ዓ.ም ሲሆን የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የገቢ፣ በጀትና ፋይናንስ እና የንግድና ኢንዱስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴዎች እንዲሁም የመንግስት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የባንኩ ፕሬዚዳንትና ም/ፕሬዚዳንቶች እንዲሁም ሌሎች የሥራ መሪዎች ተሳትፈዋል፡፡
የምክክር መድረኩን በንግግር የከፈቱት የባንኩ ፕሬዚዳንት የተከበሩ ዮሐንስ አያሌው /ፒ.ኤች.ዲ/ ባንኩ እንደ ፖሊሲ ባንክ ከተቋቋመበት ከ1901 ዓ.ም ጀምሮ ከአንድ ምዕተ ዓመት በላይ ሀገራዊ የኢኮኖሚ ሽግግርን በሚፈጥሩ የልማት ዘርፎች ላይ የተመሠረቱና በመላ ሀገሪቱ የተዘረጉ ፕሮጀክቶችን እየደገፈ በርካታ ስኬታማ ልማታዊ ለውጦችን እያስመዘገበ የመጣ ባለ ታሪክና ባለ መልካም አሻራ ባንክ ነው ብለዋል፡፡
ሆኖም ባለፉት አስር ዓመታት የመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ትግበራን ተከትሎ በነበሩ ውጫዊ እና ውስጣዊ ጫናዎች ምክንያት ባንኩ የሰጠውን ብድር ማስመለስ ተስኖት የተበላሹ ብድሮቹ ከፍተኛ ደረጃ ላይ በመድረሱ ቀጣይነቱ ላይ ጥያቄ ሆኖ ቆይቷል፡፡
በዚህ አጣብቂኝ ውስጥ መንግስት በባንኩ ቀጣይነት ላይ ከመጠራጠር ይልቅ አመራሩን እና አሠራሩን በማሻሻል በውጤታማነት ለማስቀጠል ወስኖ ታላቅ ኃላፊነት ጋራ አዳዲስ አመራሮችን ስለመመደቡም ተናግረዋል፡፡ በዚህም የቢዝነስ ሞዴል ጥናት፣ የባንኩ የገንዘብ ምንጭ ጥናት ይህንን ተከትሎም የባንኩ መዋቅራዊ አደረጃጀት ላይ ለውጦች እየተደረጉ ስለመሆናቸውም ጠቁመዋል፡፡
በማከልም በተጠናቀቀው የ2013 በጀት ዓመት ባንኩ የተበላሸ የብድር ምጣኔውን ከ34 በመቶ ወደ 26 በመቶ መቀነስ እንደቻለና ዓመታዊ የተጣራ ትርፉን ወደ ብር 3.2 ቢሊዮን ማሳደጉን ገልጸዋል፡፡
በመቀጠል የመንግስት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ትዕግስቱ አምሳሉ በበኩላቸው ባንኩ ትልቅ አሻራ ያለው ባንክ መሆኑን በመጥቀስ አጋጥሞት የነበረውን ችግር በአጭር ጊዜ ውስጥ በመሻገር ለውጤት መብቃቱ የሚደነቅ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በአጭር ጊዜ ውስጥ ለተመዘገበው ውጤትም የኤጀንሲው፣ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የገቢ፣ በጀትና ፋይናንስ ቋሚ ኮሜቴ አባላት እና ሌሎች የመንግስት አካላት ያደረጉት ድጋፍና ክትትል የጎላ ሚና እንደነበረው ጠቅሰዋል፡፡ ባንኩ የጀመረው የለውጥ ሂደት ከዚህም በላይ ሰፍቶ የተሻለ ውጤት እንዲያመጣ የተጀመረውን የአሠራር፣ የአደረጃጀት እና የአማራር ሪፎርም አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አሳስቧል፡፡ ለዚህም ኤጀንሲው የሚያደርገው ድጋፍና ክትትል ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ቃል ገብተዋል፡፡
እንዲሁም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የገቢ፣ በጀትና ፋይናንስ ቋሚ ኮሜቴ ሰብሳቢ ተወካይ ቋሚ ኮሚቴው ምንም እንኳ የባንኩ አጠራጣሪ ብድር ከፍተኛ ቢሆንም ባንኩ የጀመረው የሪፎርም ሥራ ውጤት እንደሚያመጣ በማመን ባንኩ ያቃረበውን የካፒታል ጭማሪ ጥያቄ በመንግስት ይሁንታ እንዲያገኝ በቋሚ ኮሚቴው ጥረት ሲደረግ እንደነበር ገልጸው በተለይም ባንኩ ከነ እዳቸው የተረከባቸውን ትላልቅ ፕሮጀክቶች የግብር እዳቸው በመንግስት እንዲሰረዝ ከፍተኛ ሥራ ሲሰራ እንደነበር ጨምረው አብራርተዋል፡፡
የመድረኩ ተሳታፊ የነበሩት የምክር ቤት አባላት በሰጡት አስተያየት ባንኩ የጀመራቸው የለውጥ ሥራዎች እንዳይቀለበሱ የባንኩ የሥራ አመራር ቦርድ እንዲሁም ባለድርሻ አካላት ለባንኩ የተጠናከረ ድጋፍ መስጠት እንዳለባቸው በአንክሮ አሳስበዋል፡፡
በመጨረሻም ባንኩ አሁን ለሚገኝበት ውጤት እንዲበቃ ጉልህ አስተዋጽዖ ላደረጉ ተቋማት የምስጋና ምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል፡፡
ከባለፈው እትም የቀጠለ… በመጀመሪያው ዙር ስልጠና ወስደው ያቀረቡት የቢዝነስ ዕቅድ የፀደቀላቸው ኢንተርፕራይዞች ዝርዝር ሊንኩን ተጭነው ይመልከቱ
በኤክሴል መክፈት ለማትችሉ ደግሞ የሚከተለውን ሊንክ ይጫኑ
በባንኩ ሲሰጥ የነበረው ሀገር አቀፍ ስልጠና ተጠናቀቀ
ከሰኔ 02 እስከ 06 ቀን 2013 ዓ.ም አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች በሚገኙ 12 የስልጠና ማዕከላት ለአምስት ተከታታይ ቀናት በባንኩ ሲሰጥ የቆየው ሀገር አቀፍ የአነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንተርፕራይዞች ስልጠና ሰኔ 06 ቀን 2013 ዓ.ም ተጠናቋል፡፡
ስልጠናው ከመጠናቀቁ አንድ ቀን ቀደም ብሎ ሰኔ 05 ቀን 2013 ዓ.ም የባንኩ ፕሬዚዳንት ዮሐንስ አያሌው (ፒ.ኤች.ዲ) ከአዲስ አበባና ከየስልጠና ማዕከላቱ ከሰልጣኞች ለተነሱ ጥያቄዎች በተለይም በሊዝ ፋይናንሲንግ የማሽነሪ ብድር ፖሊሲ እና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
በስልጠናው ማጠቃለያ ላይ ሰልጣኞች ስለ ስልጠናው ገንቢ አስተያየታቸውን ለግሰዋል፡፡ እንደ ሰልጣኞች አስተያየት የክህሎት ማሳደጊያ ስልጠናው ከጠበቁት በላይ ሆኖ እንዳገኙት እና ወደፊትም ከባንኩ ጋር በሚኖራቸው የሥራ ግንኙነት በእውቀት ላይ የተመሰረተ እንዲሆን እንዳስቻላቸው ገልጸው ባንኩ ይህን መሰል ስልጠና በማመቻቸቱ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
ባንኩ 2ኛውን ዙር ሀገር አቀፍ ስልጠና በይፋ ጀመረ
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ለአነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንተርፕራይዞች ያዘጋጀውን ሁለተኛውን ዙር ሀገር አቀፍ ስልጠና ሰኔ 02 ቀን 2013 ዓ.ም በይፋ ጀምሯል፡፡
በመክፈቻው መርኃ ግብር ላይ የባንኩ ፕሬዚዳንት የተከበሩ ዮሐንስ አያሌውን (ፒ.ኤች.ዲ) ጨምሮ የክልል ከፍተኛ አመራሮች፣ የባንኩ ምክትል ፕሬዚዳንቶች እና የስራ መሪዎች እንዲሁም ሰልጣኞች በአካል እና በዙም ተሳትፈዋል፡፡
የባንኩ ፕሬዚዳንት በእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግራቸው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የመንግስትን የትኩረት አቅጣጫ መሠረት በማድረግ በተለያዩ የስራ ዘርፎች ለተሰማሩ የአነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንተርፕራይዞች ከዓለም አቀፍ አበዳሪ ተቋማት ጋር በመተባበር ከ2ዐዐ7 ዓ.ም ጀምሮ ለሊዝ ፋይናንስ አገልግሎት የመካከለኛና የረጅም ጊዜ ብድር በመስጠት ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
ባንኩ ለኢንተርፕራይዞቹ እያቀረበ ያለው የገንዘብና ቴክኒክ ድጋፍ በሀገሪቱ የሚደረገውን የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር ዓላማዎችን እንዲደግፉ፣ የኢንዱስትሪ-ግብርና ጥምረትን እንዲያጠናክሩ፣ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ ሸቀጦች በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት የሚደረገውን ጥረት እንዲያግዙ፣ ሰፊ የሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ እንዲሰማሩ እና ወጪ ንግድን በማጠናከር የውጭ ምንዛሪ ግኝትን እንዲያሳድጉ ማድረግ ላይ መሠረት ያደረገ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
በዚህም መሠረት ባንኩ ከመጋቢት 13 እስከ 17 እንዲሁም ከሚያዚያ 03 እስከ 07/2013 ዓ.ም የመጀመሪያውን ዙር ስልጠና ወስደው ቢዝነስ ፕላን ካቀረቡ ኢንተርፕራይዞች መካከል ከ35ዐ በላይ ለሚሆኑ ደንበኞች ቢዝነስ ፕላናቸው የፀደቀላቸው ሲሆን የእነዚህ ደንበኞች ስም ዝርዝር ከግንቦት 28 ቀን ጀምሮ በተከታታይ በጋዜጦችና በባንኩ ድረ ገጽ ላይ በመውጣት ላይ እንደሚገኝ ጨምረው ተናግረዋል፡፡
በ2ኛው ዙርም ይህንኑ የአቅም ግንባታ የክህሎት ስልጠና በማስቀጠል በ12 የስልጠና ማዕከላት በመላው ሀገሪቱ ለሚገኙ የአነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንተርፕራዞች በተመረጡት በ7 ርዕሶች ላይ ማለትም በቢዝነስ እቅድ ዝግጅትና ርዕይ ቀረጻ፣ በቢዝነስ አመራር፣ በሰው ኃይል አስተዳደር፣ በግብይት አመራር፣ በሒሳብ መግለጫ አዘገጃጀትና እና ትንተና፣ በሀገሪቱ የቢዝነስና የፖሊሲ ከባቢያዊ ሁኔታ እና በአነቃቂ ንግግር ላይ ያተኮረ ሥልጠና መሰጠት መጀመሩና ሥልጠናው እስከ ሰኔ 06 ቀን 2013 ድረስ ለሚቀጥሉት አምስት ተከታታይ ቀናት እንደሚቀጥል ተናግረዋል፤፡
ፕሬዚዳንቱ በመጨረሻ ለሰልጣኞች ስልጠናውን በአግባቡ በመከታተል እና ወደ መሬት በማውረድ ራሳቸውን፣ ቤተሰባቸውን፣ ማህበረሰባቸውን እና ሀገራቸውን የሚጠቅም ስራ እንዲሰሩ በማሳሰብ የአደራ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
በመቀጠል የክልሎች ርዕሳነ መስተዳድሮችና ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ባንኩ ባዘጋጀው የስልጠና ማዕከላት በአካል በመገኘት መልእክታቸውን በዙም አስተላልፈዋል፡፡ እነዚህ ከፍተኛ የስራ አመራሮች የአፋር፣ ትግራይ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ሱማሌ፣ ጋምቤላ እና ሲዳማ ሲሆኑ እንዲሁ በመጀመሪያው ዙር ስልጠና ወቅት ደግሞ የኦሮሚያ፣ አማራ፣ ደቡብ እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳድር ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ያስተላለፏቸው መልእክቶች በዙም የተላለፈ ሲሆን፤ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች በሀገር ደረጃ የተጀመረውን የብልጽግና ጉዞ እውን በማድረግ ወደ ኢንዱስትሪ የሚደረገውን የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር ለማሳለጥ ዓይነተኛ ሚና እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም ስልጠናው በዕውቀት የታገዙ፣ ቀደም ሲል በዘርፉ ሲስተዋሉ የነበሩ ችግሮችን ከወዲሁ በመቅረፍ ጥራት ያላቸውና ለሥራ ፈጠራ አስተዋጽዖ ሊያበረክቱ የሚችሉ ኢንተርፕራይዞችን ለማፍራት እንደሚያግዝም አንስተዋል፡፡ የክልል የሥራ ኃላፊዎቹ ኢንተርፕራይዞቹ ስልጠናውን ከወሰዱ በኋላም ወደ ስራ በሚገቡበት ጊዜ የመስሪያ ቦታ በማመቻቸት፣ መሠረተ ልማቶችን በመዘርጋት እና ገበያን በማፈላለግ ቀጣይነት ያለውን ድጋፍ ለማድረግ ቃል የገቡ ሲሆን፤ ሰልጣኞች በበኩላቸው በሚሰጣቸውን ስልጠና ተገቢውን ግንዛቤ በመጨበጥ ለተገቢው ዓላማ ማዋል እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
Page 16 of 31