ክቡር ተገኝወርቅ ጌጡ (ፒ.ኤች.ዲ) የጃፓን ከፍተኛ የኒሻን ተሸላሚ ሆኑ!!
‹የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ የሆኑት ክቡር ተገኝወርቅ ጌጡ (ፒ.ኤች.ዲ) በጃፓን መንግስት የኒሻን ሽልማት የተሰጣቸው እ.ኤ.አ ህዳር 03 ቀን 2020 ሲሆን፤ ሽልማቱን አስመልክቶ እ.ኤ.አ መጋቢት 24 ቀን 2021 በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር መኖሪያ ቤት በተዘጋጀው ሥነ ሥርዓት ላይ ተበርክቶላቸዋል፡፡
የሀገርቷ ከፍተኛ የኒሻን ሽልማት የተበረከተላቸው በጃፓን እና በአፍሪካ እንዲሁም በጃፓን እና በኢትዮጵያ መካከል ኢኮኖሚያዊ ግንኙነቶችን በማጠናከር ረገድ ላበረከቱት አስተዋጽዖ እንደሆነ በሥነ ሥርዓቱ ላይ ተገልጿል፡፡
በእርሳቸው አመራር ሰጭነት በአፍሪካ ልማት ዙሪያ በቶክዮ ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ አማካይነት ከጃፓን መንግስት ጋር ያለውን ኢኮኖሚያዊ ግንኙነቶች ወደ ላቀ ደረጃ በማድረስ በርካታ ቢሊዮን ዶላሮች ለአፍሪካ ልማት እንዲውል ተደርጓል፡፡
በተለይም እንደ ጃፓን የውጭ ንግድ ድርጅት (ጄትሮ)፣ የጃፓን ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጄንሲ (ጃይካ)፣ UNDP እና ከኬይዛይ ዶዩዩይ (የጃፓን የኮርፖሬት አስፈጻሚዎች ማህበር) ጋር የሽርክና ማዕቀፎችን በመፍጠር የአፍሪካ ሀገራት ከጃፓን መንግስት ጋር ስትራቴጂያዊ ግንኙነት እንዲፈጥሩና በኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ክቡር ተገኝወርቅ ጌጡ (ፒ.ኤች.ዲ) ከፍተኛ አስተዋጽዖ አበርክተዋል፡፡
ሀገር አቀፍ ስልጠናው በይፋ ተጀመረ
በኢትዮጵያ ልማት ባንክ ለአነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንተርፕራይዞች ከመጋቢት 13 እስከ 17 ቀን የሚካሄደው ስልጠና ሰኞ መጋቢት 13 ቀን 2013 ዓ.ም በይፋ ተጀምሯል፡፡
ስልጠናው ሀገር አቀፍ ሲሆን በአምስት ማእከላት ማለትም በአዲስ አበባ፣ ባህር ዳር፣ ጂማ፣ ደሴና ጂግጂጋ እየተካሄደ ይገኛል፡፡
የስልጠናውን መከፈት አስመልክቶ የባንኩ ፕሬዚዳንት ዮሐንስ አያሌው (ፒ.ኤች.ዲ) ፍሬንድሺፕ ሆቴል ለአዲስ አበባ ሰልጣኞች በአካል በመገኘት እና በዙም /zoom meeting/ ደግሞ ለክልሎች መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ በመክፈቻው እለት ባስተላለፉት መልእክት በአሁኑ ሰዓት በአገሪቷ ላይ ያሉ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ዘርፈ ብዙ ችግሮችና ተግዳሮቶች እንዳሉባቸው እንደሚታወቁና ዋናዎቹ የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎችና የባለድርሻ አካላት የግንዛቤ ደረጃ አናሳ መሆን፣ ስለሊዝ ፋይናንስ የእውቀት ክፍተት መኖር፣ አንዳንድ የሊዝ ተጠቃሚዎች እንዲገዛላቸው የሚፈልጉትን የማሽነሪ ዓይነትና ጥራት ለይቶ አለማወቅ፣ አገልግሎት ፈላጊዎች የሚጠበቅባቸውን የቅድመ መዋጮ በወቅቱ አለማዋጣትና የፕሮጀክት ሃሳብ መቀያየር፣ ረጅም የሆነ የማሽነሪ የግዢ ሂደት መኖር፣ የኃይል አቅርቦት አለመኖርና የኃይል መቆራረጥ፣ የመስሪያ ቦታ ችግር፣ የባለድርሻ አካላት የተቀናጀ አገልግሎት አለመስጠት፣ የሥራ ማስኬጃ ብደር ለማግኘት የመያዣ ዋስትና ችግር እና የመሳሰሉት እንደሆኑ ገልጸው፤ ባንኩም የተለያዩ መፍትሔ እርምጃዎች በመውሰድ ላይ እንደሚገኝና ይህ ስልጠናም ግንዛቤ ከመፍጠር አኳያ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡
ስልጠናው የአነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንተርፕራይዞች ከባንኩ ጋር የሥራ ግንኙነት ከመጀመራቸው በፊት በቢዝነስ ፕላን አዘገጃጀትና ርዕይ ቀረጻ፣ በፋይናስና የሂሳብ አስተዳደር፣ ንግድ ሥራ አመራር፣ በገበያ ፍለጋ፣ በሰው ሀብት አስተዳደር፣ እንዲሁም በአጠቃላይ በሀገሪቱ የቢዝነስና የፖሊሲ ከባቢያዊ ሁኔታ እና ማበረታቻዎች ላይ አቅማቸውን በመገንባት እውቀትና ክህሎት እንዲኖራቸው ስልጠናው መዘጋጀቱን የባንኩ ፕሬዚዳንት ዮሐንስ አያሌው (ፒ.ኤች.ዲ) ጨምረው አብራርተዋል፡፡
በመቀጠል የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር የተከበሩ አቶ ሽመልስ አብዲሳ፣ የሱማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ምክትል ርዕሰ መስተዳድር የተከበሩ አቶ ሙስጠፌ መሐመድ እና በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳድር የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ የተከበሩ አቶ ጃንጥራር አባይ በዙም የመክፈቻ ንግግር አድርገዋል፡፡
ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች በንግግራቸው ባስተላለፉት መልእክት ባንኩ ይህንን ለአነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንተርፕራይዞች በእውቀት የታገዘ ስልጠና በማዘጋጀቱ አመስግነው ሌሎች መሰል የፋይናንስ ተቋማትም ይህንኑ በጎ ተሞክሮ እንዲወስዱ አሳስበዋል፡፡ በየክልላቸው ለሚገኙ የስልጠና ተሳታፊዎችም ከባንኩ ጎን በመቆም አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ስልጠናው በሀገር አቀፍ ደረጃ እንዲሁ ከመጋቢት 20 እስከ 24 ቀን 2013 ዓ.ም በአዳማ፣ ቡታጂራ እና ወላይታ ሶዶ ከተሞች የሚካሄድ ሲሆን በሁለቱ ዙር ስልጠና በአጠቃላይ ከ3500 በላይ ሰልጣኞች እንደሚሳተፉ ይጠበቃል፡፡
አርቲስት መቅደስ ፀጋዬ የባንኩ አምባሳደር ሆኖ እንድትሰራ የፊርማ ሥነ ሥርዓት ተካሄደ
አርቲስት መቅደስ ፀጋዬ ከመጋቢት 06 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ የባንኩ አምባሳደር ሆና እንድትሰራ የፊርማ ሥነ ሥርዓት በባንኩ ዋና መሥሪያ ቤት ተካሄደ፡፡
ባንኩ ተግባራዊ ማድረግ የጀመረውን የለውጥ ስራዎች ለደንበኞች፣ ባለድርሻ አካላት፣ መንግስትና ለህብረተሰቡ በተገቢው መንገድ ለማስተዋወቅና የባንኩን ገጽታ ለመገንባት እንዲቻል በህዝብ ዘንድ ተቀባይነት ያላት፣ ታዋቂ ግለሰብና አርአያ በሆነች አርቲስት መቅደስ ፀጋዬ የባንኩን አገልግሎት ማስተዋወቅ አስፈላጊ መሆኑ የውል ስምምነቱ ሲደረግ ተገልጿል፡፡
በተለይም ባንኩ ፍትሃዊና ተደራሽ የሆነ የአገልግሎት አሰጣጥ በአዲስ መልክ ተግባራዊ ለማድረግ እንቅስቃሴ በጀመረበት ወቅት ባንኩን ማስተዋወቅ የባንኩን ገጽታ ለመገንባት ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ተነስቷል፡፡
በተጨማሪም ባንኩ ለአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ተቋርጦ የነበረውን አገልግሎት በአዲስ መልክ ለመጀመር ዝግጅት በሚደረግበት ወቅት የባንኩን አገልግሎት በቋሚነት ማስተዋወቅ ለባንኩ መልካም አጋጣሚ ስለመሆኑም ተነስቷል፡፡
የውል ስምምነቱ የተፈረመው በባንኩ ም/ፕሬዝዳንት ኮርፖሬት አገልግሎት እና አርቲስት መቅደስ ፀጋዬ መካከል ሲሆን፤ በሥነ ሥርዓቱ ላይ የባንኩ ፕሬዚዳንት ተገኝተዋል፡፡
ባንኩ ለመቄዶኒያ በጎ አድራጎት ማህበር የ15 ሚሊዮን ብር
ድጋፍ አደረገ
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የስራ አመራር አባላትና ሰራተኞች በሜቄዶኒያ በጎ አድራጎት ማህበር እሁድ መጋቢት 5 ቀን 2013 ዓ.ም ባደረጉት ጉብኝት የአስራ አምስት ሚሊዮን ብር ድጋፍ የማድረግና ከ4000 በላይ ለሆኑ አረጋውያን የምሳ ማብላት መርሃ ግብር አከናውነዋል፡፡
በስነ ስርዓቱ ላይ በመገኘት የአስራ አምስት ሚሊየን ብር ቼክ ያበረከቱት የባንኩ ፕሬዝዳንት ዮሐንስ አያሌው /ፒ/ኤች.ዲ/ ሲሆኑ ባደረጉት ንግግርም የመቄዶኒያ በጎ አድራጎት ማህበር እያከናወነ ያለውን በጎ ተግባር አድንቀው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ለመቄዶኒያ የሚያደርገው ድጋፍ በዚህ ብቻ የሚቆም ሳይሆን ለወደፊትም አቅሙ በፈቀደው መጠን ከማህበሩ ጎን እንደሚቆም ተናግረዋል፡፡
የመቄዶኒያ በጎ አድራጎት ማህበር መስራችና ባለቤት የክብር ዶክተር ቢኒያም በለጠ በበኩላቸው ማህበሩ በተቸገረበት በዚህ ፈታኝ ሰዓት ላይ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ያደረገው ድጋፍ እጅግ እንዳስደሰታቸው በመግለፅ በማህበሩ እና በተረጂ ወገኖች ስም ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
Page 18 of 31