ሀገር አቀፍ ስልጠናው በይፋ ተጀመረ
በኢትዮጵያ ልማት ባንክ ለአነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንተርፕራይዞች ከመጋቢት 13 እስከ 17 ቀን የሚካሄደው ስልጠና ሰኞ መጋቢት 13 ቀን 2013 ዓ.ም በይፋ ተጀምሯል፡፡
ስልጠናው ሀገር አቀፍ ሲሆን በአምስት ማእከላት ማለትም በአዲስ አበባ፣ ባህር ዳር፣ ጂማ፣ ደሴና ጂግጂጋ እየተካሄደ ይገኛል፡፡
የስልጠናውን መከፈት አስመልክቶ የባንኩ ፕሬዚዳንት ዮሐንስ አያሌው (ፒ.ኤች.ዲ) ፍሬንድሺፕ ሆቴል ለአዲስ አበባ ሰልጣኞች በአካል በመገኘት እና በዙም /zoom meeting/ ደግሞ ለክልሎች መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ በመክፈቻው እለት ባስተላለፉት መልእክት በአሁኑ ሰዓት በአገሪቷ ላይ ያሉ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ዘርፈ ብዙ ችግሮችና ተግዳሮቶች እንዳሉባቸው እንደሚታወቁና ዋናዎቹ የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎችና የባለድርሻ አካላት የግንዛቤ ደረጃ አናሳ መሆን፣ ስለሊዝ ፋይናንስ የእውቀት ክፍተት መኖር፣ አንዳንድ የሊዝ ተጠቃሚዎች እንዲገዛላቸው የሚፈልጉትን የማሽነሪ ዓይነትና ጥራት ለይቶ አለማወቅ፣ አገልግሎት ፈላጊዎች የሚጠበቅባቸውን የቅድመ መዋጮ በወቅቱ አለማዋጣትና የፕሮጀክት ሃሳብ መቀያየር፣ ረጅም የሆነ የማሽነሪ የግዢ ሂደት መኖር፣ የኃይል አቅርቦት አለመኖርና የኃይል መቆራረጥ፣ የመስሪያ ቦታ ችግር፣ የባለድርሻ አካላት የተቀናጀ አገልግሎት አለመስጠት፣ የሥራ ማስኬጃ ብደር ለማግኘት የመያዣ ዋስትና ችግር እና የመሳሰሉት እንደሆኑ ገልጸው፤ ባንኩም የተለያዩ መፍትሔ እርምጃዎች በመውሰድ ላይ እንደሚገኝና ይህ ስልጠናም ግንዛቤ ከመፍጠር አኳያ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡
ስልጠናው የአነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንተርፕራይዞች ከባንኩ ጋር የሥራ ግንኙነት ከመጀመራቸው በፊት በቢዝነስ ፕላን አዘገጃጀትና ርዕይ ቀረጻ፣ በፋይናስና የሂሳብ አስተዳደር፣ ንግድ ሥራ አመራር፣ በገበያ ፍለጋ፣ በሰው ሀብት አስተዳደር፣ እንዲሁም በአጠቃላይ በሀገሪቱ የቢዝነስና የፖሊሲ ከባቢያዊ ሁኔታ እና ማበረታቻዎች ላይ አቅማቸውን በመገንባት እውቀትና ክህሎት እንዲኖራቸው ስልጠናው መዘጋጀቱን የባንኩ ፕሬዚዳንት ዮሐንስ አያሌው (ፒ.ኤች.ዲ) ጨምረው አብራርተዋል፡፡
በመቀጠል የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር የተከበሩ አቶ ሽመልስ አብዲሳ፣ የሱማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ምክትል ርዕሰ መስተዳድር የተከበሩ አቶ ሙስጠፌ መሐመድ እና በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳድር የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ የተከበሩ አቶ ጃንጥራር አባይ በዙም የመክፈቻ ንግግር አድርገዋል፡፡
ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች በንግግራቸው ባስተላለፉት መልእክት ባንኩ ይህንን ለአነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንተርፕራይዞች በእውቀት የታገዘ ስልጠና በማዘጋጀቱ አመስግነው ሌሎች መሰል የፋይናንስ ተቋማትም ይህንኑ በጎ ተሞክሮ እንዲወስዱ አሳስበዋል፡፡ በየክልላቸው ለሚገኙ የስልጠና ተሳታፊዎችም ከባንኩ ጎን በመቆም አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ስልጠናው በሀገር አቀፍ ደረጃ እንዲሁ ከመጋቢት 20 እስከ 24 ቀን 2013 ዓ.ም በአዳማ፣ ቡታጂራ እና ወላይታ ሶዶ ከተሞች የሚካሄድ ሲሆን በሁለቱ ዙር ስልጠና በአጠቃላይ ከ3500 በላይ ሰልጣኞች እንደሚሳተፉ ይጠበቃል፡፡
አርቲስት መቅደስ ፀጋዬ የባንኩ አምባሳደር ሆኖ እንድትሰራ የፊርማ ሥነ ሥርዓት ተካሄደ
አርቲስት መቅደስ ፀጋዬ ከመጋቢት 06 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ የባንኩ አምባሳደር ሆና እንድትሰራ የፊርማ ሥነ ሥርዓት በባንኩ ዋና መሥሪያ ቤት ተካሄደ፡፡
ባንኩ ተግባራዊ ማድረግ የጀመረውን የለውጥ ስራዎች ለደንበኞች፣ ባለድርሻ አካላት፣ መንግስትና ለህብረተሰቡ በተገቢው መንገድ ለማስተዋወቅና የባንኩን ገጽታ ለመገንባት እንዲቻል በህዝብ ዘንድ ተቀባይነት ያላት፣ ታዋቂ ግለሰብና አርአያ በሆነች አርቲስት መቅደስ ፀጋዬ የባንኩን አገልግሎት ማስተዋወቅ አስፈላጊ መሆኑ የውል ስምምነቱ ሲደረግ ተገልጿል፡፡
በተለይም ባንኩ ፍትሃዊና ተደራሽ የሆነ የአገልግሎት አሰጣጥ በአዲስ መልክ ተግባራዊ ለማድረግ እንቅስቃሴ በጀመረበት ወቅት ባንኩን ማስተዋወቅ የባንኩን ገጽታ ለመገንባት ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ተነስቷል፡፡
በተጨማሪም ባንኩ ለአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ተቋርጦ የነበረውን አገልግሎት በአዲስ መልክ ለመጀመር ዝግጅት በሚደረግበት ወቅት የባንኩን አገልግሎት በቋሚነት ማስተዋወቅ ለባንኩ መልካም አጋጣሚ ስለመሆኑም ተነስቷል፡፡
የውል ስምምነቱ የተፈረመው በባንኩ ም/ፕሬዝዳንት ኮርፖሬት አገልግሎት እና አርቲስት መቅደስ ፀጋዬ መካከል ሲሆን፤ በሥነ ሥርዓቱ ላይ የባንኩ ፕሬዚዳንት ተገኝተዋል፡፡
ባንኩ ለመቄዶኒያ በጎ አድራጎት ማህበር የ15 ሚሊዮን ብር
ድጋፍ አደረገ
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የስራ አመራር አባላትና ሰራተኞች በሜቄዶኒያ በጎ አድራጎት ማህበር እሁድ መጋቢት 5 ቀን 2013 ዓ.ም ባደረጉት ጉብኝት የአስራ አምስት ሚሊዮን ብር ድጋፍ የማድረግና ከ4000 በላይ ለሆኑ አረጋውያን የምሳ ማብላት መርሃ ግብር አከናውነዋል፡፡
በስነ ስርዓቱ ላይ በመገኘት የአስራ አምስት ሚሊየን ብር ቼክ ያበረከቱት የባንኩ ፕሬዝዳንት ዮሐንስ አያሌው /ፒ/ኤች.ዲ/ ሲሆኑ ባደረጉት ንግግርም የመቄዶኒያ በጎ አድራጎት ማህበር እያከናወነ ያለውን በጎ ተግባር አድንቀው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ለመቄዶኒያ የሚያደርገው ድጋፍ በዚህ ብቻ የሚቆም ሳይሆን ለወደፊትም አቅሙ በፈቀደው መጠን ከማህበሩ ጎን እንደሚቆም ተናግረዋል፡፡
የመቄዶኒያ በጎ አድራጎት ማህበር መስራችና ባለቤት የክብር ዶክተር ቢኒያም በለጠ በበኩላቸው ማህበሩ በተቸገረበት በዚህ ፈታኝ ሰዓት ላይ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ያደረገው ድጋፍ እጅግ እንዳስደሰታቸው በመግለፅ በማህበሩ እና በተረጂ ወገኖች ስም ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
ታላቅ የምስራች በአነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ ስራ ላይ ለተሰማራችሁ እና ለወደፊቱ እቅዱ ላላችሁ የቀረበ የሥልጠና ማስታወቂያ ጥሪ
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የመንግስትን የትኩረት አቅጣጫ መሠረት በማድረግ በማኑፋክቸሪንግ፣ በአግሮ ፕሮሰሲንግ፣ በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ፣ በማዕድን ልማት፣ በቱሪዝም ኢንዱስትሪ፣ በእርሻ እና በአግሪካልቸራል መካናይዜሽን አገልግሎት የሥራ ዘርፎች ለተሰማሩ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የሊዝ ፋይናንሲንግ አገልግሎት /የማምረቻ መሣሪያ አቅርቦት በስፋት ሲሰጥ መቆየቱ ይታወቃል፡፡
ባንኩ አሰራሩን በአዲስ መልክ በማዘመን እና ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት በመስጠት አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ሀገሪቱ ከግብርና መር ኢኮኖሚ ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለምታደርገው መዋቅራዊ ሽግግር የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ በመሆኑ ኢንተርፕራይዞች የበለጠ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እና የሚሰሩትን ሥራ በዕውቀት ላይ የተመሰረተ ለማድረግ ባንኩ በቢዝነስ ፕላን ዝግጅት እና አስቀድሞ የድርጅትን ራዕይ የማስቀመጥ፣ የፋይናንሽያል ዝግጅትና ትንተና፣ የቢዝነስ አስተዳደር፣ የሰው ኃብት አመራር፣ የገበያ ጥናት፣ የፖሊሲ ቅኝት እንዲሁም የሊዝ ፋይናንሲንግ አሰራር የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ለመስጠት ዝግጅቱን አጠናቋል፡፡
ሥልጠናው በስምንት ማዕከላት ማለትም በአዲስ አበባ፣ ባህር ዳር፣ ጂግጂጋ፣ ደሴ እና ጅማ ከመጋቢት 13 እስከ 17 ቀን 2013 ዓ.ምእንዲሁምበአዳማ፣ ወላይታ ሶዶ እና ቡታጅራ ከተሞች ላይ ደግሞ ከመጋቢት 20 እስከ 24 ቀን 2013 ዓ.ም የሚካሄድ ይሆናል፡፡
ሥልጠናውን እንዲወስዱ የታሰቡ ተሳታፊዎች 1ኛ) ከባንኩ የፕሮጀክትና የሊዝ ፋይናንሲንግ አገልግሎት እያገኙ ያሉና በሥራ ላይ የሚገኙ ኢንተርፕራይዞች 2ኛ) ለመሳተፍ ቢዝነስ ፕላን ለባንኩ ያቀረቡ ወይም ለማቅረብ የተዘጋጁ 3ኛ) እውቀቱ፣ ሙያው እና አቅሙ ያላቸው ቢዝነስ ፕላን ለማዘጋጀት የሚፈልጉ እና ዝቅተኛውን መስፈርት አሟልተው የባንኩን ድጋፍ የሚፈልጉ አዲስ ኢንተርፕራይዞችንም ጭምር ይመለከታል፡፡
የሊዝ ፋይናንሲንግ አገልግሎት ከባንኩ ለማግኘት በቅድሚያ ባንኩ ያዘጋጀውን ይህንን ሥልጠና መውሰድ ባንኩ ለሚሰጠው አገልግሎት እንደ ቅድመ ሁኔታ የሚወሰድ መሆኑ ታውቆ ምዝገባውን ያከናወናችሁ ኢንተርፕራይዞች በሙሉ ከላይ በተጠቀሰው ቀን እና ቦታ ተገኝታችሁ ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት ሥልጠናውን በአግባቡ እንድትከታተሉ ባንኩ በአክብሮት ይጋብዛል፡፡
ሥልጠናው የሚመለከተው የድርጅቱ ባለቤት ወይም ዋና ሥራ አስኪያጅ ወይም ከድርጅቱ የውክልና ደብዳቤ የሚያቀርብ ሲሆን ሃሳብ እና ፍላጎቱ ብቻ ያላቸው ማሳሰቢያው አይመለከታቸውም፡፡
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ፣ የልማት አጋርዎ!!
Page 13 of 26