ባንኩ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሄደ
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የአነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንተርፕራይዞችን ፋይናንስ ለማድረግ ያለመ ውይይት ከመንግስትና የግሉ ዘርፍ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር መጋቢት 01 ቀን 2013 ዓ.ም በቢሾፍቱ ከተማ አካሂዷል፡፡
በውይይቱ ላይ የባንኩ ፕሬዚዳንት፣ ምክትል ፕሬዚዳንቶችና ዲስትሪክት ስራ አስኪያጆች እንዲሁም የፌዴራል እና ክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የአምራች ዘርፍ፣ የግል ባንኮች እና አነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት የሥራ መሪዎች ተገኝተዋል፡፡
ስብሰባውን በንግግር የከፈቱት የፌዴራል አነስተኛ መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ልማት ማስፋፊያ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ አስፋው አበበ እንዳሉት ለሀገር በቀል ኢኮኖሚ ትልቅ ተስፋ የተጣለበትን አነስተኛ መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ልማት ፋይናንሲንግ ዙሪያ ለመነጋገር በተዘጋጀው በዚህ መድረክ ላይ ፋይናንስ ለኢንዱስትሪው ዘርፍ ልማት የደም ስር መሆኑንና ያለ ፋይናንስ የኢንዱስትሪውን ልማት ከፍ ማድረግ እንደማይቻል ጠቅሰዋል፡፡
የውይይት መድረኩ መዘጋጀት ዋነኛ ዓላማ አነስተኛና መካከለኛ አምራች ዘርፎችን ፋይናንስ በማድረግ ሂደት ያጋጠሙ ችግሮችን ከአሠራርና ከአፈጻጸም አኳያ በመገምገም ችግሮቻቸውን ማስተካከል በሚቻልበት ዙሪያ እና ተቋርጦ የነበረውን የማሽነሪ ሊዝ ፋይናንሲንግ ውጤታማ በሆነ መንገድ ፋይናንስ ለማድረግ በዓለም ባንክ ለዘርፉ የተደረገውን የ8.6 ቢሊዮን ብር ድጋፍ በአግባቡ ለመጠቀም የባለድርሻ አካላት ቅንጅት ለማምጣት መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ አብራርተዋል፡፡
በአምራች ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ላይ ተሰማርተው የፋይናንስ፣ የቴክኖሎጂ፣ የመስሪያ ቦታ እና የገበያ ትስስር ክፍተት ያለባቸውን ኢንተርፕራይዞች ችግር ለማቃለል የተገኘውን ሀብት በአግባቡ ለመጠቀም ተቀናጅቶ መስራት ወሳኝ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዝዳንት ዮሐንስ አያሌው /ፒ.ኤች.ዲ/ በበኩላቸው በተለያዩ ምክንያቶች ተቋርጦ የቆየውን የካፒታል ዕቃ ኪራይ አገልግሎት በአዲስ መልክ ለመጀመር ቀደም ሲል ዘርፋን ሲያጋጥሙ የነበሩ ችግሮችን በመቅረፍ ብድር ወደመስጠት ለመሄድ ደንበኞች መብትና ግዴታቸውን እንዲያውቁና ስለሚሰሩት ሥራ በቂ ግንዛቤና ራዕይ ሊኖራቸው ስለሚገባ ባንኩ በሰባት ማዕከላት ስልጠና ለመስጠት ቅድመ ዝግጅት ማጠናቀቁን ገልጸዋል፡፡
ባንኩ ከስልጠና በኋላ ለሚሰጠው የማሽነሪ ሊዝ ፋይናንስ፣ የሥራ ማስኬጃ ብድር (Working capital) እና የፕሮጀክት ብድር ባለድርሻ አካላት ከባንኩ ጎን በመሆን አስፈላጊውን ትብብር ማድረግ እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡ በተለይም ቀደም ሲል ሲስተዋል የነበረውን የቅንጅት ችግር በመቅረፍ በተናበበና በትብብር መንፈስ አምራች ዘርፉን መደገፍ እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡
በመድረኩ ላይ የተገኙት ባለድርሻ አካላት በሰጡት አስተያየት በአጭር ጊዜ ውስጥ ባንኩ ተግባራዊ እያደረገ ያለውን የሪፎርም ሥራ በማድነቅ ባንኩ የሚሰራቸውን ሥራዎች በግንባር ቀደምትነት ለመደገፍ ያላቸውን ቁርጠኝነት ገልጸዋል፡፡
የአነስተኛ መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ልማት ለማስፋፋት የዛሬ አራት ዓመት መንግስት በሰጠው አቅጣጫ ከጥቃቅንና አነስተኛ ወደ አነስተኛና መካከለኛ የተሸጋገሩ (the missing middle) ኢንተርፕራይዞች የፋይናንስ ችግር ለመፍታት በርካታ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ሰፊ ውይይት ተደርጎ የተጀመረ ሥርዓት መሆኑ ይታወሳል፡፡
ባንኩ ዓለምአቀፍ የሴቶች ቀንንአ ከበረ
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ሰራተኞች ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀንን /March 8/ የካቲት 29 ቀን 2013 ዓ.ም በባንኩ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ያከበሩ ሲሆን፤ የባንኩን ፕሬዚዳንት ጨምሮ ምክትል ፕሬዚዳንቶች እና የባንኩ ሰራተኞች ተገኝተዋል፡፡
በሥነ ስርዓቱ የባንኩ መሰረታዊ ሰራተኞች ማህበር የሴቶች ተወካይ ወ/ሮ ኦሪት አበበ በባንኩ ውስጥ ሴቶች ያላቸው የአመራርነት ድርሻ አነስተኛ በመሆኑ ለወደፊቱ ሴቶችን የማብቃትና ወደ ኃላፊነት የማምጣት ተግባር ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ተግባር መሆኑን አንስተዋል፡፡
የባንኩ ፕሬዚዳንት ዮሐንስ አያሌው /ፒ.ኤች.ዲ/ በበኩላቸው በባንኩ ውስጥ የሴቶች ቁጥር በአመራር ቦታ አነስተኛ መሆኑን እና በባንኩ ውስጥ እየተከናወነ ባለው የሪፎርም ስራ ላይ በአንጽዖት እንደሚታይ ቃል ገብተዋል፡፡
በመጨረሻም የባንኩን ሴቶች በመወከል ንግግር ያደረጉት ወ/ሮ አልማዝ ጥላሁን እንዳሉት የሴቶች ቀን ሲከበር የበዓሉን ማክበር ብቻ ሳይሆን ሴቶች ላይ የሚደርሱ አሉታዊ ተጽዕኖዎችና ጥቃቶችን በመከላከል ሴቶችን ለተሻለ ውጤት በማብቃት ጭምር መሆን እንዳለበት ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የባንኩ BSC ወርክሾፕ ላይ የማጠቃለያ መርኃ ግብር ተካሄደ
ባንኩ ከየካቲት 08-17/2013 ዓ.ም ሲያካሂድ የነበረውን አዲስ የውጤት ተኮር ምዘና ስርዓት ስልጠና /BSC/ የማጠቃለያ መርኃ ግብር የካቲት 26 ቀን 2013 ዓ.ም በባንኩ የመሰብሰቢያ አዳራሽ አካሂዷል፡፡
በማጠቃለያ መርኃ ግብሩ ላይ የባንኩ ፕሬዚዳንትን ጨምሮ ም/ፕሬዚዳንቶች ዳይሬክተሮችና የቡድን ሥራ አስኪያጆች የተገኙ ሲሆን፤ የዲስትሪክት እና ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጆች በዙም /zoom meeting/ ስብሰባውን ተሳትፈዋል፡፡
ስብሰባውን በንግግር የከፈቱት የባንኩ ፕሬዚዳንት ዮሐንስ አያሌው /ፒ.ኤች.ዲ/ ሲሆኑ እንደርሳቸው ገለጻ ይህ የውጤት ተኮር ምዘና /BSC/ ወርክሾፕ ባንኩ ለጀመረው የሪፎርም ስራ አንዱ አጋዥ መሳሪያ ነው ብለዋል፡፡
ባንካችንን ደረጃውን የጠበቀ ባንክ /world class/ ለማድረግ የሚያስችል ቢዝነስ ሞዴል እየተዘጋጀ መሆኑን እንዲሁም ተግባራዊ እየተደረገ ባለው ባንኩ የጀመረውን ለውጥ ውጤታማ እንዲሆን ለማድረግ ሁሉም የስራ መሪና ሰራተኛ ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ እንደሚገባም ጨምረው ተናግረዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ ቀሪ ጊዜ ውስጥ የተጀመረውን የሪፎርም ሥራ በሚፈለገው ጥራትና ፍጥነት ለማከናወን በውጤት ተኮር የምዘና ሥርዓት /BSC/ መታገዝ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በተለይም ባንኩ የብድር አሰባሰብ ማሳደግ፣ የተበላሸ የብድር ምጣኔ መቀነስ፣ የተቀላጠፈ አገልግሎት መስጠት እና ጥራት ያለው የብድር አሰጣጥ ተግባራዊ ማድረግ ላይ በውጤት ተኮር የምዘና ሥርዓት ታግዞ መስራት ለውጤት እንደሚያበቃ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ መጨረሻም ሆነ በቀጣዮቹ ተከታታይ ዓመታት የባንኩን የተበላሸ የብድር ምጣኔ ለመቀነስ እንዲቻል የተጀመረውን ሪፎርም ስራ ማጠናከር እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የባንኩ የውጤት ተኮር ምዘና (BSC) ከባንኩ የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ ተቆርሶ እስከ ሠራተኛ ድረስ የሚወረድበት አሠራር ለመዘርጋት በከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲከለስ መደረጉን አብራርተዋል፡፡
የተከለሰውን የውጤት ተኮር ምዘና በአጭር ጊዜ ውስጥ ተግባራዊ ለማድረግ ይቻል ዘንድም በሶስት ማዕከላት ማለትም በባንኩ ዋና መ/ቤት፣ በባህርዳርና ሀዋሳ ስልጠናዎች ሲሰጡ እንደነበር ተናግረዋል፡፡
ለሪፎርሙ መሳካትም 7 ስትራቴጂክ ምሶሶዎች፣ 26 ስትራቴጂክ ዓላማዎች እና ቁልፍ የአፈፃፀም አመልካቾች ሠራተኛ ድረስ በማውረድ ባንኩ ውስጥ ግልጽነት እና ተጠያቂነት እንዲሰፍን ለማድረግ ታስቦ እየተሰራበት እንደሚገኝ አክለው ገልጸዋል፡፡
የባንኩ የማሻሻያ ስራዎች ቀጣይነታቸው እንዲረጋገጥ በትኩረት መስራት እንደሚያስፈልግ የገንዘብ ሚኒስቴር ገለጸ
- የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ባለፉት ስድስት ወራት ያከናወናቸው ዋና ዋና የማሻሻያ ስራዎች የባንኩን ትርፋማነት ለማሳደግ እንዳስቻለ ተገልጿል፡፡
በገንዘብ ሚኒስትሩ በክቡር አቶ አህመድ ሽዴ በተመራ ግምገማ ላይ እንደተገለጸው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ትርፋማነቱ ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በብር 304.16 ሚሊዮን ብልጫ ማለትም በ150 በመቶ ከፍ ያለ ሆኖ ተገኝቷል፡፡
አቶ አህመድ ሽዴ የባንኩ ትርፋማነት የተገኘው ተለያዩ የለውጥ ስራዎች በመተግበራቸው እንደሆነ በግምገማው ወቅት አብራርተዋል:: በተለይም ባንኩ የነበረውን ብድር የማስተዳደርና የመቆጣጠር አቅም ማሳደጉ ለዚህ ውጤት እንዳበቃው ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም የኢትዮጵያ የልማት ባንክ በስድስት ወር ውስጥ የህዳሴ ግድብ ቁጠባን በተመለከተ ብር 500 ሚሊየን ለመፈፀም አቅዶ ብር 883.47 ሚሊየን ለመሰበብሰብ መቻሉ የሚበረታታ መሆኑም በግምገማው ተመልክቷል፡፡ በተለይም ኢትዮጵያዊያን በራሳቸው አቅም እየገነቡት ያለው የህዳሴ ግድብ ወቅቱን ጠብቆ ማጠናቀቅ እንዲቻል ባንኩ ጥረቱን አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባው ክቡር አቶ አህመድ ሽዴ አሳስበዋል፡፡
የኢትዮጵያ ልማት ባንክን የማሻሻያ ስራዎች ውጤታማነታቸውን ቀጣይ ለማድረግ ባንኩ በአዳዲስ እና በቴክኖሎጂ የታገዙ የአሰራር ስርዓቶችን ማጎልበት፣ የባንኩን የውጭ ምንዛሪ አቅም ማሳደግ እና የባንኩን አማራጭ የሀብት ምንጭ ለማጎልበት የሚያስችሉ ተግባራት ቀዳሚ ትኩረት የሚሹ መሆናቸውን አቶ አህመድ ሽዴ አስረድተው፤ ባንኩን በዘላቂነት ከሀብት ጥገኝነት ለማውጣት የማሻሻያ ስራዎች በወጣላቸው መርሀ ግብር መሰረት መተግበር እንደሚኖርባቸውም ማሳሰባቸው ታውቋል፡፡
Page 14 of 26