ባንኩ የአረጋውያን እና አቅመ ደካሞች የቤት እድሳት ፕሮግራም አስጀመረ
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በቂርቆስ እና ጉለሌ ክፍለ ከተሞች የሚገኙ 11 የአረጋውያን እና አቅመ ደካሞች ቤቶችን እና 1 መጸዳጃ ቤት የዕድሳት ማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓት ነሐሴ 18 እና 19 ቀን 2013 ዓ.ም አከናውኗል፡፡
የአረጋውያን እና አቅመ ደካሞች ቤት ለዕድሳት ሥራው ሲፈርስ
በሥነ ሥርዓቱ ላይ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት የተከበሩ ዮሐንስ አያሌው (ፒ.ኤች.ዲ)፣ የባንኩ ምክትል ፕሬዚዳንቶች እና የሥራ መሪዎች፣ የየክፍለ ከተሞቹ ዋና ሥራ አስፈጻሚዎች፣ የወረዳ አመራሮች፣ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች እና የአካባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል፡፡
ለቤት ዕድሳት የተመረጡትን ቤቶች የማፍረስና እድሳቱ በማስጀመር ሥነ ሥርዓት ላይ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት ዮሐንስ አያሌው (ፒ.ኤች.ዲ) ባደረጉት ንግግር በኢትዮጵያ ልማት ባንክ በኩል ተግባራዊ የሚደረጉ ፕሮጀክቶች በዋናነት እንዲያካትቷቸው ከሚገደዱባቸው መሥፈርቶችም አንዱ ማኅበራዊ ኃላፊነትን መወጣት እንደመሆኑ ባንካችን ለሀገር ዋጋ የከፈሉትን ማሰብና ለሀገራቸው የዋሉት ውለታ በከንቱ እንዳልነበር ማስታወስ አስፈላጊ ብቻ ሳይሆን ግዴታም ነው ብሎ የሚያምን በመሆኑ በዚህ የቤት ዕድሳት መርኃ ግብር ላይ ተሳታፊ ሆኗል ብለዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ በንግግራቸው ለሀገር ውለታ በመዋል ስሌት የዕድሜ ጠገብ አረጋውያን ያህል መታወስና መመስገን ያለበት አካል የለም ያሉ ሲሆን፤ አያይዘውም ባንካችን የአረጋውያንን እና አቅመ ደካሞችን ቤት ለማደስ ያደረገው ድጋፍ ባንኩ ለሀገር ባለውለታ አረጋውያን እና አቅመ ደካሞች ያለውን ትኩረት ማሳያ ጅምር ሥራ መሆኑን፣ ሀገር የህልውና አደጋ ላይ ስትሆን ደግሞ ባንኩ ሀገራዊ ጥሪዎችንም በመቀበል ለሀገር መከላከያ ሠራዊት እንዲሁ ከ96 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉን ገልጸው፤ ለወደፊቱም ይህን ተልዕኮ አጠናክሮ በመርህና በዕቅድ ስለሚሠራ ባንኩ ለሚሠራው ሥራ ሁሉ ሁሉም አካላት ተባባሪ እንዲሆኑ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡
የጉለሌ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አባወይ ዮሐንስ እና የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ምክትል ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተጫነ አዱኛ በበኩላቸው ባንኩ ከልማት ሥራዎቹ ጎን ለጎን የአቅመ ደካሞችን እና የአረጋውያን ቤት ለማደስ እያደረገ ያለውን ያላሰለሰ ጥረት በማድነቅ ለወደፊቱም አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ጠይቀዋል፡፡
የቤት ዕድሳቱ መርኃ ግብር ተጠቃሚ የሆኑ አረጋዊያን እና አቅመ ደካሞች በበኩላቸው ባንኩ በችግራቸው ጊዜ ደራሽ ሆኖ ስላገኙት ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
ታላቅ የምስራች ለአነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች!!
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በመላ ሃገሪቱ የሚገኙ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የሊዝ ፋይናንስ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በሁለት ዙር ለ 5,111 ኢንተርፕራይዞች የክህሎት ማሳደጊያ ስልጠና የሰጠ ሲሆን በአንደኛው ዙር ከሰለጠኑት ሰልጣኞች መካከል 349 ለሚያህሉት ኢንተርፕራይዞች ያቀረቡት የቢዝነስ ዕቅድ በባንኩ መመዘኛ መስፈርት ተገምግሞ ተቀባይነት በማግኘቱ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ለመሆን በሂደት ላይ ይገኛሉ፡፡
ባንካችን በ2014 በጀት ዓመት ወደ ሥራ ለሚገቡ የራሳቸው ማምረቻ ቦታ ካላቸው ወይም ከመንግስት አካል የማምረቻ ሼድ ካገኙት ኢንተርፕራይዞች በተጨማሪ በባንኩ መስፈርት መሰረት አዋጭ የቢዝነስ ፕላን አዘጋጅተው መስፈርቱን ላሟሉ እና በኪራይ ቦታ ለመስራት በሚመለከተው አካል የተመዘገበ የማምረቻ ቦታ ኪራይ ውል ማቅረብ ለሚችሉ ኢንተርፕራይዞች አገልግሎቱን ለመስጠት የወሰነ መሆኑን በታላቅ ደስታ ይገልጻል፡፡
ለተጨማሪ መረጃ በአቅራቢያችሁ ወደሚገኙ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ቅርንጫፎች በመቅረብ ዝርዝር መረጃውን ማግኘት የምትችሉ መሆኑን እናስታውቃለን፡፡
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ፣ የልማት አጋርዎ!!
Page 9 of 26